መረጃን ከትክክለኛው ምንጭ በማግኘት በተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡ ማድረስ ይገባል…የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ

110
ህዳር 19/2011 ሁሉም መገናኛ ብዙሀን ትክክለኛ የዜና ምንጭ ናቸው ብሎ መውሰድ እንደማይገባና መረጃን ከትክክለኛው ምንጭ በማግኘት በተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ገለጹ፡፡ በማህበራዊ ሚድያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን መለየት በሚቻልበት ሂደት ላይ ለጋዜጠኞች ስልጠና ተሰጠ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአልጃዚራ ሚድያ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በማህበራዊ ሚድያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን እንዴት ለይቶ መጠቀም እንደሚቻል እና ከሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች የግንዛቤ መስጫ ስልጠና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት የአልጃዚራ ሚድያ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሞንታሰር ማራይ በማህበራዊ ሚድያዎች የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች ግጭት መቀስቀስ፤የተቋማት ወይም ግለሰቦችን ስም በማጥፋት በማህበረሰቡ ውስጥ ጥርጣሬ በማሳደር ሀገርን ወዳልተፈለገ ቀውስ የመምራት አቅም ስለሚኖራቸው እውነተኛውን የዜና ምንጭ በአግባቡ መለየት እንደሚገባ ነው የጠቀሱት፡፡ ሀሰተኛ መረጃዎች በአረቦች አብዮት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል የሚሉት የአልጃዚራ ሚድያ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሞንታሰር ትክክለኛ ዜናን መለየት ላይ ብዙ ርቀት መሄድ ያስፈልጋል ሲሉ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡ ሀሰተኛ መረጃው አንዴ ከተለቀቀ በኋላ ቢታረም እንኳን ምልዕክቱ በማህበረሰቡ ውስጥ ስለሚሰረጭ በሚድያ ተቋሙ ላይ የተዓማኒነት ችግር ሊፈጥር ስለሚችል መገናኛ ብዙሀን ዜናውን ለተደራሹ ከመልቀቃቸው በፊት የመረጃውን ይዘት በጥንቃቄ ማየት፤የተለያዩ ምንጮችን መመልከት፤እና የኤዲቶሪያል እይታ ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡ ጋዜጠኞች የመረጃ ምንጭን በሚገባ መመርመር እና ትክክለኛነቱን አረጋግጠው በመጠቀም ሊደርስ የሚችልን ጉዳት መቀነስ እንደሚችሉ ሞንታሰር ማራይ የአልጃዚራን ተሞክሮ አብራርተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በስልጠናው ወቅት ባደረጉት ንግግር የማህበራዊ ሚድያ እድገት ክስተት መሆኑን ጠቅሰው መረጃን ከትክክለኛው ምንጭ በማግኘት በተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡ ማድረስ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ”ሁሉም መገናኛ ብዙሀን ትክክለኛ የዜና ምንጭ ናቸው ብሎ መውሰድ አይገባም”ያሉት ቃል አቀባዩ በተለይ ከውጭ ምንጮች የሚገኙ መረጃዎችን አግባብነት ማረጋገጥ፤ከሀገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ለህብረተሰቡ ማድረስ ይገባል ብለው ፤ጋዜጠኞች ደግሞ ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም