በወተትና በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚገጥማቸውን ችግር የሚፈታ ግብረ-ኃይል ተቋቋመ

121
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 በወተት ማምረትና በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ግብረ-ኃይል ተቋቋመ። ግብረ-ኃይሉ ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን በግብርናና እንስሳት ኃብት ሚኒስቴር የሚመራ መሆኑ ተገልጿል። በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተዘጋጀና በወተትና ዶሮ እርባታ ዘርፍ ያሉ ዋና ዋና ችግሮችና መፍትሄዎችን የሚጠቁም ጥናት ለዘርፉ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በጥናቱ የመኖ፣ የህክምናና የመድሃኒት አቅርቦት፣ የመሰረተ ልማትና የመሬት አቅርቦት ችግር በዘርፉ እየተስተዋሉ እንደሆነ ተገልጿል። ከውይይቱ በኋላም ችግሮቹን በቅንጅት ለመፍታት የሚረዳ ግብረ-ኃይል ተቋቁሟል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ የወተት አምራቾች ማህበራት ቦርድ አባል አቶ ካሳ አበበ በዘርፉ የመኖ እጥረት እየገጠማቸው መሆኑን ይናገራሉ። በዚህም ሳቢያ የወተት ምርት እጥረት እንደገጠመ ገልፀው ችግሩን ለመፍታት መንግስት የቁጥጥር ተግባር ሊያከናውን ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ የዶሮ አርቢዎችና አቀነባባሪዎች ማህበር የቦርድ አባልና የግብረ-ኃይሉ አባል አቶ አሸናፊ ደስታ ዘርፉ የመኖ አቅርቦት፣ የመድሃኒትና የክትባት ችግር እየገጠመው መሆኑን ገልፀዋል። የተቋቋመው ግብረ-ኃይልም በዘርፉ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ተባብሮ ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የእንስሳት መኖ ኢንዱስትሪ ማህበር አባል አቶ አለማየሁ አሳየ በበኩላቸው የመኖ እጥረት የተፈጠረው ህገ-ወጥ ደላሎች መኖ በማከማቸትና ጊዜ ጠብቆ በውድ ዋጋ በመሸጥ ያለአግባብ ትርፍ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረትና ከፋብሪካ የሚወጡና ለመኖ ግብዓት የሚውሉ ተረፈ ምርቶች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ በመጣሉ ምክንያት ነው ይላሉ። የተቋቋመው ግብረ-ኃይልም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን የሚፈታ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል። በኢትዮጵያ ከፍተኛ የቁም እንስሳት እምቅ ኃብት ቢኖርም አገሪቱ በሚፈለገው መጠን ጥቅም አላገኘችም ያሉት ደግሞ የግብርናና የእንስሳት ኃብት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ ናቸው። ዘርፉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመደገፉና የቅንጅት ችግር በመኖሩ ምክንያት አገሪቱ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል ነው ያሉት። የእንስሳት ኃብት ምርታማነትን ለማሳደግና የግብዓት ችግርን ለማስተካከል በትኩረት ይሰራል ብለዋል። በጥናቱ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታተ የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ገልፀው በቀጣይም በቅንጅት የሚፈቱ ይሆናሉ ነው ያሉት። ግብረ-ኃይሉ የዘርፉን ችግሮች ለማስተካከል እንደሚረዳ የገለጹት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ሁሉም የመፍትሄ አካል መሆኑን ተረድቶ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ከ15 እስከ 17 በመቶ ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት፤ 10 በመቶ ደግሞ ለአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ አስተዋፅኦ እንዳለው በጥናቱ ተገልጿል። በአገሪቱ አንድ ሰው በዓመት 19 ሊትር ወተት፣ ስምንት እንቁላል እንዲሁም 0 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም የዶሮ ስጋ እንደሚመገብ በጥናቱ ተጠቁሟል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም