አነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት የሃገሪቱን ልማት እያገዙ መሆናቸው ተገለጸ

60
መቀሌ ህዳር 19/2011 የአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን በኩል የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናስ አቅራቢ ተቋማት ማህበር ገለጸ። አገር አቀፍ የአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት አመታዊ የምክክር መድረክ ዛሬ በመቐለ ከተማ ተጀምሯል። የማህበሩ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ከበደ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በሀገራችን ያሉት የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት በጥቃቅነና አነስተኛ ስራ ለሚተዳደሩ አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ ቀላል አይደለም። በተለይም ለባንክ ተደራሽ ያልሆነ የከተማም ሆነ የገጠር ማህበረሰብ ተደራሽ በመሆን የስራ እድል ፈጠራና ምርታማነትን ለማሳደግ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሆነ ተናግረዋል። የትግራይ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል አሰፋ በበኩላቸው እንዳሉት አነስተኛ የፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ህብረተሰቡ በልማቱ የሚኖረውን ተሳትፎ ለማጎልበት ያላቸው ሚና እየጎላ መጥቷል። “በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኘው የማህበረሰብ ክፍልና ለወጣቶች ፋይናንስ በማቅረብ እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም” ብለዋል። “በፋይናንስ አገልግሎት የተሰማሩ ተቋማት በስራቸው የሚያጋጥሟቸውን ጠንካራና ደካማ ጎኖች አንስተው መመካከራቸው በቀጣይ ጠንካራ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል” ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሰታፊና የዘርፉ ባለሞያ አቶ ሳምሶን ግዛው ናቸው። መድረኩ ለፖሊሲ አውጪዎች ጭምር የሚጠቅም በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባው ገልጸው በባለሙያዎች የሚቀርቡ ጥናቶችም ለፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ቀጣይ ስራ አቅም እንደሚሆኑ ጠቁመዋል። በውይይት መድረኩ በየክልሉ ያሉት የአነስተኛ የፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት የሁለት ዓመታት የስራ እንቅስቃሴ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል። ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የምክክር መድረክ በሀገራችን የሚገኙ አነስተኛ የፋይናንስ አቅራቢ ተቋማትና በዚሁ ዙሪያ ምርምርና ጥናት የሚያደርጉ አካላትን ጨምሮ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም