ለኢትዮ-ኤርትራ ወዳጅነት መጠናከር ሁለቱ መንግስታት የጀመሩትን ጥረት እናግዛለን---የአፋር ክልል የጸጥታ አካላት

60
አፋር ህዳር 19/2011 በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በሁለቱ መንግስታት የተጀመረውን ጥረት እንደሚያግዙ የአፋር ክልል የጸጥታ አካላት ገለጹ። የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር የጋዥነት ሚናውን እንደሚወጣም የክልሉ የጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል። በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሰሞኑን በተካሄደው የክልል አቀፍ የጸጥታ አካላት የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል የጸጥታ አካላት እንደገለጹት በሁለቱ አጎራባች ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ግንኙነት እንዲጠናከር ይሰራሉ። የቢዱ ወረዳ አስተዳደር ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህንድ አብዱቃደር የአፋር ክልል ከኤርትራ ጋር ሰፊ ድንበር የሚጋራና ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተፈጥሮ በነበረው የሰላም እጦት ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም በላይ የአፋር ህዝብ ተጎጂ እንደነበር ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ በተፈጠረው የሰላም ስምምነት ተቋርጦ የነበረው የየብስና አየር ትራንስፖርት ግንኙነት በመጀመሩ የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት ያጠናከረ መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ የዳሎል፣ ቢዱና አፍዴራ ወረዳ ነዋሪዎች ከ100 እስከ150 ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ አስመራና አሰብ መድረስ ቢቻልም በኤርትራ በኩል በተሽከርካሪ መግባት ስለማይፈቀድ ዘመድ ጥየቃ 400 ኪሎ ሜትር በዛላንበሳና ቡሬ በኩል እንዲያቋርጡ መገደዳቸውን ተናግረዋል። "ህብረተሰቡ ላላስፈላጊ እንግልትና ለከፍተኛ ወጭ እየተዳረገ ነው" የሚሉት ኃላፊው ለሁለቱ ህዝቦች መልካም ጉርብትና መጠናከር ሲባል በሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የዳሉል ወረዳ አስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሃጂ አህመድ አብደላ ወረዳው ከኤርትራ ድንበር የሚዋሰንና በሃይማኖትም ሆነ ባህል የተሳሰረ አንድ ህዝብ የሚኖርበት መሆኑን ጠቅሰው በተፈጠረው ሰላም ህብረተሰቡ መደሰቱን ተናገረዋል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግስት የአጋዥነት ሚናውን እንዲወጣ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡ የአፋር ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡመር ኩቲና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ መሪነት በሁለቱ አገራት የተፈጠረው ሰላም  ለአፋር ህዝብ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኃላፊው “የአፋርና የኤርትራ ህዝብ ቤተሰባዊ ትስስር እንዲጠናከር ጥረት ይደረጋል” ብለዋል፡፡ መንገድ ባለባቸው አካባቢዎች ህዝቡ ግንኙነት ማድረግ አንዲችል ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት ስራዎች እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም