ፌዴራል ዋና ዳኛ ጌቱ ተፈራ ለ 1 ዓመት ከ 6 ወር ከእግር ኳስ ዳኝነት እንዲታገዱ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው

78
አዲስ አበባ ህዳር 19/2011 ፌዴራል ዋና ዳኛ ጌቱ ተፈራ ለ 1 ዓመት ከ 6 ወር ከእግር ኳስ ዳኝነት እንዲታገዱ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው። ዳኛው እገዳ የተጣለባቸው በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም በጎንደር ስታዲየም በፋሲል ከተማና በሐዋሳ ከተማ ክለቦች መካከል በተካሄደ ጨዋታ በሰሩት የቴክኒክ ስህተት መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ውሳኔው የጨዋታው ዋና ዳኛ የነበሩት ጌቱ ተፈራን አስመልክቶ የጨዋታው ኮሚሽነር  ባቀረቡት የአፈጻፀም ሪፖርት እንዲሁም ዋና ዳኛው ጨዋታውን በመሩበት ወቅት ስለፈፀሙት የቴክኒክ ስህተት ያቀረቡትን የይቅርታ ደብዳቤ መሠረት ያደረገ ነው ተብሏል። በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ጥቅምት 27 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል። ኮሚቴው ፌዴራል ዋና ዳኛ ጌቱ ተፈራ የፈፀሙት ከፍተኛ የቴክኒክ ስህተት "ከአንድ ሲኒየር ፌዴራል የእግር ኳስ ዳኛ የማይጠበቅ ጥፋት" መሆኑን ገልጿል። ከጨዋታው ፍጻሜም በኋላ የፈፀሙትን  የቴክኒክ ስህተት በማመንና ለወደፊቱም ከዚህ ዓይነት ድርጊት ተቆጥበው የሚመደቡበትን ጨዋታ በአግባቡና በትክክል ለመምራት የሚዘጋጁበት መሆናቸውን ፌዴራል ዋና ዳኛ ጌቱ ተፈራ በጽሑፍ ማረጋገጣቸው ተጠቅሷል። በዚሁ መሰረት ኮሚቴው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የእግር ኳስ ዳኞች፣ ኢንስትራክተሮችና ታዛቢዎች የሥነ-ስርዓት እርምጃ ደንብ መሠረት ለ1 ዓመት ከ6 ወር ከእግር ኳስ ዳኝነት እንዲታገዱ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ውሳኔው ጌቱ ተፈራ በፌዴራል ዳኛነት ማገልገል ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የሚያስቀጣ ስህተት ፈጽመው የማያውቁና ባሳዩት የአፈፃፀም መሻሻል በኤሊት ዳኛነት ውስጥ መግባታቸውን  እንዲሁም እስከዚህ ጨዋታ ድረስ የነበራቸውን መልካም አፈፃፀም ከግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነም ተጠቅሷል። ፌደራል ዋና ዳኛ ጌቱ ተፈራ በፋሲል ከተማና በሀዋሳ ከተማ ጨዋታ 87ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ የፋሲል ከተማው ኤፍሬም አለሙ ላይ ጥፋት ተሰርቷል በማለት ፊሽካ ካሰማ በኋላ የፋሲል ከተማው ሽመክት ጉግሳ በጨዋታ እንቅስቃሴ በማስቆጠሩ ግቡን አጽድቋል። በውሳኔው ከሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ጋር በተፈጠረው አለመግባባትም ጨዋታዉ ከ20 ደቂቃ በላይ ተቋርጦ ቆይቶ በመጨረሻም የፍጹም ቅጣት ምቱ እንዲመታ ሆኗል። የፍጹም ቅጣት ምቱ በመሰጠቱም ከሀዋሳ ተጫዋቾች ጋር የተፈጠረው ግርግር የሀዋሳ ከተማው ተጫዋች አዳነ ግርማ በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ የሚታወስ ነው። ፌደራል ዳኛው የሰጡትን ፍጹም ቅጣት ምት ሽመክት ጉግሳ ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን በአጠቃላይ ጨዋታው በፋሲል ከተማ 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈራ በ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ ድሬዳዋ ከተማ ሆሳዕና ከተማን 3 ለ 1 ያሸነፈበትን የፍጻሜ ጨዋታ በብቃት በመምራት 6 ሺህ ብር ተሸላሚም ነበሩ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም