ቲቦር ናጊ ለሶስት ቀናት ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

57
አዲስ አበባ ህዳር 19/2011 የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ። በቆይታቸውም በኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነትና በስድስተኛው የአሜሪካ-አፍሪካ ህብረት የከፍተኛ አመራሮች ውይይት ላይ ይሳተፋሉም ተብሏል። የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ቲቦር ናጊ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከአዲሱ ሹመታቸው በኋላ የመጀመሪያ እንደሆነም ነው የተገለፀው። አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የኢኮኖሚና ዲሞክራሲ ለውጥ እንደምትደግፍና የአፍሪካ ኀብረት በአጀንዳ 2063 ያቀደውን ከግብ ለማድረስ ድጋፏን እንደምትቀጥልም ተገልጿል። ቲቦር ናጊ እ.አ.አ ከ1999 እስከ 2002 ድረስ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ናቸው። የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ እንደሚያብራራው የቲቦር ናጊ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በምስራቅ አፍሪካ የሚያደርጉት ጉብኝት አካል ነው።  ረዳት ሚኒስትሩ በአሜሪካና በአፍሪካ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ከህዳር 18 እስከ ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራና ኬንያ እንደሚያደርጉ መገለፁ ይታወሳል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም