የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተ ልማት ግንባታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር እገዛ ማድረጉ ተገለጸ

70
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 በኢትዮጵያ ካለፉት ጊዜያቶች በተሻለ መልኩ በኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተ ልማት ጥሩ ለውጥ ከማሳየትም ባሻገር በህዝቦች መካከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገለጹ። ኤሌክትሪክና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት፣ ምርትን ወደ ገበያ ለማውጣት፣ ህዝቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ይታመናል። በዚህም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እድገቷ አዎንታዊ ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝም ብዙዎች ይስማማሉ። በኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተ ልማት ግንባታ በህዝቡ ኑሮ ለውጥ በማሳየት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ዶክተር አሰፋ አድማሴ የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያ ኢትዮጵያ የምታመርተው ኤሌክትሪክ በቂ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ የህዝብን ኑሮ ለውጧል ብዬ አስባለው በተለይ በፊት ኤሌክትሪክ የማይደርስባቸው አካባቢዎች አሁን ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክን ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ጀምራለች። ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ህዝብ ብቻ ሳይሆን በተለይ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለጎረቤት አገሮች መዳረሱ ከኢኮኖሚው ባሻገር ትልቅ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ ዶክተር ካሳ ተሻገር በበኩላቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን እየሰራች ነው ፣እንደዚሁም  የፓወር ትራንስሚሽን መስመር ወደ ኬንያ፣ ሱዳንና ወደ ተለያዩ አገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ኤክስፖርት ለማድረግ እየሰራች ነው ያለችው፣ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ እቅድ ጋር ተያይዞ እየሰራች ያለቻቸው ስራዎች መልካም ስሟን ሰጥተዋታል ሲሉ ገልጸዋል። የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው ካለፉት ሁለት አስርት አመታት ወዲህ በኤሌክትሪክ ሃይል ግንባታ ውጤትና ለውጥ እየተመዘገበ ቢሆንም በቂ ባለመሆናቸውና ከፍላጎቱ ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። አቶ አብርሃም ሳሙኤል የተባሉ አስተያየት ሰጭ እንደገለጹት"እጅግ አናሳና ለህዝቡ የማይዳረሱ የነበሩ መሰረተ ልማቶች ከሁለት አስርት አመታት ወዲህ በአስገራሚ ሁኔታ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ተሰርተዋል፤ ይሁን እንጂ አሁንም የመብራት መቆራረጦች በየቀኑ የሚያጋጥሙ በመሆናቸው ህብረተሰቡ በዚህ ላይ እርካታ አላገኘም ይህም ቶሎ መስተካከል አለበት።" አቶ ማሞ ወርዶፋ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ጉዳይ በፊት በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ አሁን ቢቆራረጥም ከፊተኛው እየተሻሻለ መጥቷል  ብለዋል፡፡ በውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደገለጹት፤ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ላይ የኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅምን ወደ 17ሺ 347 ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው። በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት ዓቅም 4ሺ 284 ሜጋ ዋት መድረሱን ጠቁመዋል። ዕቅዱን ለማሳካት ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከጸሃይና ከሌሎች የኃይል አመራጮች ለማመንጨት የግል ባለሃብቶችን ባሳተፈ መልኩ ለመስራት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል። የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የገናሌ ዳዋ 3፣ የረጲ ደረቅ ቆሻሻ፣ የኮይሻ የሃይል ማመንጫ እንዲሁም አይሻ 2 የንፋስ ሃይል ማመንጫ በግንባታ ላይ ካሉት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም