ህዋዊ አገር አቀፍ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውድድር ሊያካሂድ ነው

119
አዲስ አበባ ህዳር 19/2011 የቻይናው ቴሌኮምኒኬሽንና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች አምራች ህዋዊ በኢትዮጵያ ተማሪዎችና መምህራን ያሳተፈ አገር አቀፍ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ውድድር ሊያካሂድ ነው። በአገር ወስጥ የሚገኙ ከ20 ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች እና መምህራን በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ህዋዊ ውድድሩን የሚያካሂደው ከቻይና ኤምባሲ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሚያካሂድ ህዋዊ በኢትዮጵያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ለተማሪዎች እና መምህራን በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ያላቸዉን ብቃት ለመገምገም ውድድሩ እንደተዘጋጀ ተገልጿል። የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውድድሩ ከመንግስት፤ ትምህርትና ኢንዱስትሪ የተዋቀረ ሐሳብ የተለያዩ ጥቅሞችን ከማበርከትም ባሻገር በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች እዉነተኛ የሕይወት ልምድ እንዲያገኙ እንደሚያስችልም በመግለጫው ተመልክቷል። የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የተሻለ ሥርአተ ትምህርት ለማዳበር እና ተማሪዎችን የወደፊት የቅጥር እድሎችን ለማዘጋጀት ውድድሩ እንደሚረዳ ተገልጿል። ለተማሪዎች የተለየ የትምህርት ልምድ ከመስጠትም ባሻገር በአገራቸዉ ተወዳድረዉ ለዓለም አቀፍ ዉድድር ተመራጭ እንዲሆኑ እድል እንደሚሰጣቸው የህዋዊ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቴድ ሜንግዩ ተናግረዋል። የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዉድድር አላማ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን አዳዲስ ክህሎቶችንና እዉቀት ይፋ በማድረግ የኢትዮጵያን መገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማሳደግ እና ብቁ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት ነዉ ብለዋል። ትናንት ውድድሩን አስመልክቶ በትምህርት ሚኒስቴር ግቢ ዉስጥ ህዋዊ  የዉድድሩን መክፈቻ ምርቃት ፕሮግራም በማድረግ የዉድድሩን ሶስት ክፍሎች ይፋ አድርጓል። የምርቃት ፕሮግራሙን በመቀጠል ህዋዊ ዉድድሩን ለማስተዋወቅ የሚሆኑ ዝግጅቶች (የበራሪ ወረቀት ስርጭት፤ ትላልቅ የማስተዋወቂያ ሰሌዳዎችን መስቀል እና የመንገድ ትርኢት ማነቃቂያ ስራዎች) ያካሂዳል። ዉድድሩ ሶስት ደረጃዎች ሲኖሩት ይህም አንደኛ፣ መካከለኛ እና የመጨረሻ ደረጃዎችን እንደሚያካትትና እያንዳንዱ የትምህርት ተቋም የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፈተናዎችን በማካሄድ ሶስት ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ብቁ ተማሪዎችን ይመርጣል። እነዚህ ተማሪዎችን ደግሞ የህዋዊ ተወካዮች በተገኙበት የመካከለኛ ደረጃ ዉድድር እንዲወዳደሩ እንደሚደረግና ከዚያም ከመካከለኛ ደረጃ ዉድድር 20 ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ብቁ ተማሪዎችን በመምረጥ ለመጨረሻ ደረጃ ዉድድር እንዲሳተፉ ይደረጋል። ከመጨረሻ ደረጃ ዉድድር 6 ከፍተኛ ነጥብ ያላቸዉ ተማሪዎች ተመርጠዉ ደግሞ 3 የመጨረሻ ብቁ ተማሪዎች በሽልማት ፕሮግራም ላይ እዉቅና እንደሚሰጣቸው ከህዋዊ ኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም