የትምህርት ፍኖተ ካርታው ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥቷል - የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

102
ጎንደር ህዳር 18/2011 በብሄራዊ የትምህርት ፍኖተ ካርታው ለአካል ጉዳተኞች የከፍተኛ ትምህርት እድል ተጠቃሚነት ትኩረት መሰጠቱን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም ተናገሩ፡፡ የጎንደር ዩንቨርሲቲ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካቶ ትምህርት ፕሮግራም አካል ጉዳተኞችን የከፍተኛ ትምህርት ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረውን ፕሮግራም የሚገመግም አለም አቀፍ ኮንፍረንስ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ በኮንፍረንሱ ላይ ሚኒስትሯ እንደተናገሩት በሀገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹ የመማሪያ አካባቢ በመፍጠር በኩል ሰፊ ክፍተቶች አሉባቸው፡፡ "ተቋማቱ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ድጋፍ የሚያደርግ ምቹ ስርአት ያልዘረጉ በመሆናቸውም በትምህርት ቆይታቸው ስኬታማ ሆኖ ለማጠናቀቅ ችግር ይገጥማቸዋል" ብለዋል፡፡ ለቀጣዮቹ 25 አመታት እንዲያገለግል እየተዘጋጀ ያለው ብሄራዊ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ችግር ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል፡፡ "አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከሌሎች ተማሪዎች እኩል የትምህርት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግም የአካቶ ትምህርት ፕሮግራም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲተገበር በትኩረት ይሰራል" ብለዋል፡፡ "የጎንደር ዩንቨርሲቲ የጀመረው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የአካቶ ትምህርት ፕሮግራም ወደ ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስፋፋበትንና ዩንቨርሲቲውም በዘርፉ የልህቀት ማእከል ሆኖ እንዲቀጥል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል፡፡ የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ እንደተናገሩት ዩንቨርሲቲው ለቀጣዮቹ 10 አመታት የሚቆይ የአካል ጉዳተኞች የአካቶ ትምህርት ፕሮግራም ካለፈው አመት ጀምሮ 60 ተማሪዎችን በመቀበል ማስተማር ጀምሯል፡፡ ዩንቨርሲቲው የተቀበላቸው አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ሲሆን በቀጣዮቹ 10 አመታትም 450 አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምር ተናግረዋል፡፡ "ፕሮግራሙ በምስራቅ አፍሪካ በኤርትራ፣ በጂቡቲ፣ በሱማሌና በሱዳን የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያሰለጥን ገልጸው ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያም በካናዳ ሀገር ከሚገኘው ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የ24 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝቷል" ብለዋል፡፡ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የቦርድ ሊቀ-መንበር ሚስተር ጂም ሊች በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ በቀጣዮቹ አመታት የከፍተኛ ትምህርት እድል ያላገኙ 30 ሚሊዮን አፍሪካውያን አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱን ተናግረዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ ከጎንደር ዩንቨርሲቲ ጋር የጀመረውን ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ሚስተር ጂም ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ብቁ መምህራንን በማሰልጠን የአቅም ግንባታ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የጎንደር ዩንቨርሲቲ በጀመረው የአካል ጉዳተኞች የአካቶ ትምህርት ፕሮግራም በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃግብር የ2ኛ አመት ትምህርቱን የሚከታተለው ተማሪ ገብረኪዳን ሽባባው ባገኘው ነጻ የትምህርት እድል መደሰቱን ተናግሯል፡፡ "የትምህርት እድሉን ባላገኝ ኖሮ እንደሌሎች የአካባቢዬ አካል ጉዳተኞች በቤት ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ኑሮን እገፋ ነበር" ያለው ተማሪ ሽባባው የወደፊት ህይወቴ የተቃና እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልኛል" ብሏል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የፕሮግራም ግምገማ ኮንፍረንስ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የጎንደር ዩንቨርሲቲ አመራሮችና መምህራን ተገኝተዋል፡፡ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን አባላትና የፕሮግራሙ ተጠቃሚ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችም ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም