በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከ7 ሺህ ለሚበልጡ የአይን ህሙማን ነፃ የህክምና አገልግሎት ተሰጠ

66
ማይጨው ሚያዝያ 25/2010 አልባሳር ኢንተርናሽናል ፈውንዴሽን የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በትግራይ ደቡባዊ ዞን ለሚገኙ ከ7ሺህ በላይ የአይን ህሙማን ነፃ የህክምና አገልግሎት ሰጠ፡፡ ፋውንዴሽኑ በማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል ለአንድ ሳምንት ያህል የህክምና አገልግሎቱን የሰጠው ከትግራይ ጤና ጥበቃ ቢሮ ጋር በመተባበር ነው፡፡ በለምለም ካርል ማይጨው ሆስፒታል የአይን ሞራ ቀዶ ህክምና ባለሞያ አቶ የማነ ግተት እንደገለጹት ከፋውንዴሽኑ ጋር በመተባበር በሆስፒታሉ ለ10ሺህ ያህል ሰዎች የአይን ህክምና ለመስጠት ታቅዶ ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ የሆስፒታሉ ባለሙያዎችና የፋውንዴሽኑ 16 ከፍተኛ የአይን ህክምና ቡድን አባላት ለአይን ህሙማን የመድሃኒት፡ የመነፅርና የአይን ሞራ ገፈፋ ህክምና መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ በአልባሳር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ አስተባባሪ መምህር ያሲን ራጁ በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ በአፍሪካና ኤሽያ ሀገራት ውስጥ 29 የአይን ህክምና ሆስፒታሎችን በማቋቋም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች በነጻ የአይን ህክምና ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል የተሰጠው የህክምና እርዳታም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመድሃኒትና መሳሪያዎችን ግዢ ጨምሮ ለአጠቃላይ ህክምናው ፋውንዴሽኒ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የአልባሳር ኢንተርናሽናል ፈንድ ኦፊስ ማናጀር ሚስተር ፋክሩዲን ዳካን በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ለሚያካሂደው የአይን ህክምና ለማጠናከር በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ 11 የአይን ህክምና መስጫ ሆስፒታሎችን ለመገንባት ማቀዱን ገልፀዋል፡፡ ከሚገነቡት ሆስፒታሎች መካከል በ800 ሚሊዮን ብር ወጪ የአዲስ አበባ የአይን ህክምና ማሰልጠኛና ሆስፒታል ግንባታ እንደሚገኝበት ተናግረዋል፡፡ በአይን በሽታ ለረጅም ግዜ ማየት ተስኗቸው የቆዩና አሁን ባገኙት የህክምና አገልግሎት የአይን ብርሀናቸው እንደሚመለስ ተስፋ እንዳገኙበት  የተናገሩት ደግሞ የአገልግሎቱ ተጠቃሚና የጨርጨር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ በላይነሽ አሊ ናቸው፡፡ በአይናቸው በደረሰባቸው ህመም ማየት ሲቸገሩ እንደቆዩ የተናገሩት ደግሞ የአምባላጌ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሓረጎት ኪሮስ ናቸው፡፡ አሁን በተደረገላቸው ቀዶ ጥገና ህክምና የአይናቸው ብርሃን በመመለሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ የእንዳመሆኒ ወረዳ ነዋሪ ሼክ ሓያት ፈረጃ በበኩላቸው በአይን ህመም ምክንያት ለአራት አመታት ያህል ማየት ተስኑዋቸው እንደቆዩ ገልጸዋል፡፡ አሁን በተደረገላቸው  ህክምና ማየት በመጀመራቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ በትግራይ ክልል በሚገኙ ከተሞች በተለያየ ምክንያት ማየት ተስኗቸው ለነበሩ ከ40 ሺህ በላይ ወገኖች ነፃ የአይን ህክምና መስጠቱ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም