ኢትዮጵያ የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦት ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት መስራት አለባት ተባለ

479

አዲስ አበባ ህዳር 18/2011 የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርትንና ጤናን ጨምሮ የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ለማጠናከር በትኩረት መስራት እንዳለበት የዓለም ባንክ አሳሰበ።

ጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ ንጹህ መጠጥ ውሃና የገጠር መንገድ ልማት በመሰረታዊ አገልግሎት ዘርፍ ከሚካተቱ የማህበራዊ ልማት አውታሮች መካከል  ናቸው።

በመንግስትና የልማት አገሮች ትብብር በእነዚህ የልማት ዘርፎች በኢትዮጵያ የሚካሄዱ መርሃ-ግብሮች የእስካሁን ትግበራን በጋራ ለመገምገም የተዘጋጀ ስብስባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የዓለም ባንክ የጤና ዘርፍ ከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ባለሙያና የሰው ኃብት ልማት መርሃ ግብር ሃላፊ ሚስ አን ባኪላና ኢትዮጵያ መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት የተለያዩ ማዕቀፎችና መርሃ ግብሮች በመቅረጽ እየሰራች እንደሆነ ይገልጻሉ።

ያም ቢሆን አገሪቱ ካላት መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና ብዝሃነት አንጻር የአገልግሎት አሰጣጡ ተደራሽነትና ተጠቃሚነት በስፋት ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም አክለዋል።

ከፌደራል እስከ ክልል ባሉ መዋቅሮች መሰረታዊ አገልግሎቶች ዘላቂነት ባለው መልኩ መስጠት የሚቻልበት ስርዓት ሊጠናክር እንደሚገባና መዋቅሩ እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ የዘለቀ መሆኑም መረጋገጥ እንዳለበት አመልክተዋል።

ለመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦት የሚውለው ገንዘብ ለታለመት ዓላማ መዋሉን የሚያረጋግጥ ጠንካራ የፋይናንስ ቁጥጥር ስርአት ሊኖር እንደሚገባም ነው ሚስ አን ባኪላና ያሳሰቡት።

በተጨማሪም በመሰረታዊ አገልግሎቶች ልማት ላይ ማህበራዊ ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲሰፍን፤ ህብረተሰቡም በአገልግሎቶቹ ልማትም ሆነ አስተዳደር ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግም ይገባል ብለዋል።

ባለፉት 15 እና 20 ዓመታት ኢትዮጵያ በጤናና ትምህርት ውጤታማ የልማት ሥራዎችን ያከናወነች ቢሆንም በአገልግሎቶቹ  ላይ የሚታየውን የጥራት ችግር ለመቀነስ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅባትም አሳስበዋል።

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማትን እና መሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦትን ለማስፋት ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚጠበቅበትን ድጋፍም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እዮብ ተካልኝ ኢትዮጵያ በመሰረታዊ የአገልግሎት አቅርቦት ላይ ጥሩ የሚባሉ ተግባራትን ያከናወነች ቢሆንም አገልግሎቱን ዘላቂ ከማድረግ አንጻር ግን አሁንም ችግር እንዳለ ያነሳሉ።

ለዚህም አንዱ ምክንያት የሰው ሀብት ልማቱ እድገት በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑን የተነሳ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህንን የተገነዘበው መንግሰትም ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሰው ሀብት ልማት ችግሩ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪና የጤና ባለሙያ ከማፍራት ጋር የተያያዘ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዲኤታው ይህንንም ለመፍታት መንግስት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

በአገልግሎት አቅርቦት ላይ ያለውን የፋይናንስ ስርአት ለማጠናከርና ስርአቱን በቴክኖለጂ የማስደገፍ ጅምር ስራዎች እንዳሉና ይህም በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራበት አመልክተዋል።

የመሰረታዊ አገልግሎቶችን አቅርቦት ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካል በትብብርና በተቀናጀ መንገድ መስራት እንዳለበት ሚኒስትር ዲኤታው አሳስበዋል።

የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦት ተግባራዊነትን በጋራ ለመገምገም የተዘጋጀው ስብስባ እስከ ህዳር 21 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።

በስብሰባው በመንግስትና የልማት አጋሮች አማካኝነት ጽሁፎች ይቀርባሉ፤ ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ላይም ውሳኔዎች ይተላለፋል።