ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና ድንገተኛ ጉዳቶችን የመከላከልና የማከም ክፍተት አለ

85
አዲስ አበባ ህዳር 18/2011 በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና ድንገተኛ ጉዳቶችን ለመከላከልና ለማከም ክፍተት እንዳለ በጥናት መረጋገጡን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ድንገተኛ ጉዳቶች ኮሚሽን አስታወቀ። የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ድንገተኛ ጉዳቶችን መከላከልና ማከም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጿል። ኮሚሽኑ ከጤና ሚኒስቴርና ከባለድርሻ አካለት ጋር ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎችና ድንገተኛ ጉዳቶች ዙሪያ አውደ ጥናት አካሂደዋል። የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር አብርሃም ኃይለመልዓክ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ ለሆነ ህልፈተ ህይወት ምክንያቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና ድንገተኛ ጉዳቶችን መከላከልና ማከም ላይ ያለ ክፍተት ነው። ክፍተቶቹ በፋይናንስ አመዳደብ ፣ በህክምና ተቋማት ዝግጅትና አቅም እንዲሁም ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ አስፈላጊውን ድጋፍ አለማድረግ እንደሆነም በጥናት ተረጋግጧል። የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር ፣ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ማቀናጀት ፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን መከታተል፣ መቆጣጠርና ሰፋፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መስራት ከመንግስት እንደሚጠበቅም የጥናቱ ምክረ ሀሳብ እንደሆነ ተገልጿል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ 235 የበሽታ መከላከያና ማከሚያ መለኪያዎች ውስጥ 90ዎቹ በጥናቱ የተለዩና ማን ምን ይስራ? የሚለውም ተቀምጧል ሲሉም አብራርተዋል። የኮሚሽኑ ፀሐፊ ዶክተር ውብአየ ዋለልኝ በበኩላቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ድንገተኛ ጉዳቶች የተሰጣቸው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ በኀብረተሰቡ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያደረሱ ይገኛሉ ብለዋል። ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ ጫት መቃም፣ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ለበሽታዎቹ እንደሚያጋልጡም  ጠቁመዋል። በሽታዎቹን ለመከላከል የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር፣ አዋጭ የሆኑ አገልግሎቶችን ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት፣ የተመረጡ የጤና ፓኬጆችን ውጤታማ በሆነ መልኩ መተግበርና ወጪ ቆጣቢ የቅድመ መከላከል አገልግሎቶችን ማስፋፋት ተገቢ ነው ሲሉም አብራርተዋል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት ሚኒስቴሩ ከኮሚሽኑ ያገኘውን ጥናት እንደ ግብዓት በመጠቀም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ድንገተኛ ጉዳቶችን ለመከላከልና ለማከም ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። ሚኒስቴሩ የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ በመሆኑም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን በመከላከልና የአገልግሎት ሽፋኑን በማሳደግ ውጤት ማስመዝገቡንም ተናግረዋል። ውጤት ከተመዘገበባቸው ተላላፊ በሽታዎች መካካል ወባ፣ ቲቢ፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስና ትኩረት የሚሹ ትሮፒካል በሽታዎች እንደሆኑም አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት ከህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ከአማካይ የዕድሜ ጣራ መጨመር፣ ከከተሞች መስፋፋት፣ ከአኗኗር ዘይቤ ለውጥና ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ እየተስፋፉ ያሉትን በሽታዎችን ለመከላካልም የተለያዩ ተግባራት ቢከናወኑም አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ ገልጸዋል። በተለይም ክፍተቶቹ በመሰረተ ልማት ውስንነት፣ በመድኃኒትና በህክምና ቁሳቁሶች አለመሟላት ፣ ለውሳኔ የሚያግዝ የመረጃና የግንዛቤ እጥረት እንዲሁም የባለሙያዎች ክህሎት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። የኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ድንገተኛ ጉዳቶች ኮሚሽን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2016 የተቋቋመ ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም