በህገ-ወጥ መንገድ ዘይትና ስኳር ሲያጓጉዙ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

78
ደብረብርሀን ህዳር 18/2011 በሰሜን ሽዋ ዞን በህገ-ወጥ መንገድ ዘይትና ስኳር ሲያጓጉዙ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በ7 ዓመት ከስምንት ወር ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ። በፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወይዘሮ ዘርትሁን ያዘው ለኢዜአ እንዳስታወቁት ፍርድ ቤቱ ሚፍታህ ኢብራሂምና አንተነህ ለገሰ በተባሉ ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው መንግስት በድጎማ የሚያቀርበውን ስኳርና ዘይት በህገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ በመገኘታቸው ነው። ነዋሪነቱ ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ሚዳ ወረዳ የሆነው ሚፍታህ ኢብራሂም  ጥር 7 ቀን 2010 ዓ.ም ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ20 በአንድ ኤፍ ኤስ አር የጭነት መኪና 499 ባለ 20 ሊትር ጀሪካ ዘይትና ሁለት ኩንታል ስኳር ጭኖ ሲጓዝ ደብረ ብርሃን ከተማ መያዙን ተናግረዋል። የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆነው ሌላው ተከሳሽ አንተነህ ለገሰ በበኩሉ የካቲት 17 ቀን 2010 ዓ.ም  እኩለ ሌሊት ላይ  በአይሱዚ የጭነት መኪና 360 ባለ 20 ሊትር ጀሪካ የምግብ ዘይት በህገወጥ መንገድ ጭኖ  ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በጉዞ ላይ እያለ አጣዬ ከተማ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል፡፡ ግለሰቦቹ በፈፀሙት ወንጀል ጥፋተኛ መሆናቸው በሰውና በሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ህዳር 13 እና 14 ቀን 2011 በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በ7 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እስራትና በ8 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የተወሰነባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ስኳርና ዘይቱን ሲያጓጉዙ የተገኙት ተሽከርካሪዎችም ለባለቤቶቻቸው እንዲመለስ የተደረገ ሲሆን በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የተገኘው ስኳርና ዘይት ለመንግስት ገቢ እንዲሆን መወሰኑን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም