በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዩኒዬኖች ዘንድሮ 79 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገኘት አቅደው እየሰሩ ነው - ኤጄንሲው

67
አዳማ ህዳር 18/2011 በኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ዩኒዬኖች 79 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማስገኘት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን የክልሉ ህብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጄንሲ ገለፀ። የኤጄንሲው ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ለኢዜአ እንደገለጹት የህብረት ሥራ ዩኒዬኖች ገቢውን ለማስገኘት ያቀዱት ከአርሶ አደሩ የሚረከቡትን የግብርና ምርት አቀነባብረውና በጥሬው ለውጭ ገበያ በማቅረብ ነው፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት በዩኒዬኖች አማካይነት ወደ ውጪ ከተላከው የግብርና ምርት 47 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል። ቡና፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ከተላኩ የግብርና ምርቶች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ምርቱ በዋናነት ወደ መካክለኛው ምስራቅ፣ ህንድ፣ ፓኪስታንና የአውሮፓ ሀገራት መላካቸውን አቶ ዳኛቸው ተናግረዋል። በዘንድሮ ዓመትም 79 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገኘት ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ በግብርና ምርት ማቀነባበር ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ከ70 በላይ ዩኒዬኖች ከአርሶ አደሩ የሚረከቡትን ምርት በጥሬውና እሴት ጨምረው ወደ ውጪ በመላክ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ላይ ከሚገኙት መካከልም የኦሮሚያ ቡና አምራች የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን፣ ጋለማ፣ መቂ ባቱ፣ ሉሜ አዳማ፣ በቾ ወልሶና ሄጦሳ ዩኒዬኖች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። የሚላከውን  የምርት ጥራት ለማስጠበቅ ዩኒዬኖችን ብቃትና አቅም ባለው የሰው ሃይል ከማጠናከር ጀምሮ ለአርሶ አደሩ ስልጠና መሰጠቱንም ጠቅሰዋል። ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የጤፍና የስንዴ ዱቄት በማቀነባበር ወደ ተለያዩ ሀገራት እየላኩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሉሜ አዳማ ህብረት ሥራ ዩኒዬን ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብዲ ናቸው። በተጨማሪም የጥራጥሬ እህሎችን በተለይም ነጭና ቀይ ቦሎቄ እንዲሁም ሽንብራን ወደ መካከለኛ ምስራቅና ኤሲያ ሀገራት መላክ መጀመራቸውን ተናግረዋል። ''በዘንድሮ ዓመትም በጥሬና የተቀነባበረ የግብርና ምርቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመላክ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከክልሉ መንግስት ጋር በትብብር እየሰራን እንገኛለን'' ብለዋል። ''የሽንኩርትና ቲማቲም ምርቶችን ወደ ጅቡቲ፣ ሱማሊ ላንድና ፑንት ላንድ እየላክን ነው'' ያሉት ደግሞ የመቂ ባቱ ህብረት ሥራ ዩኒዬን ሥራ አስኪያጅ አቶ ያዴሳ ገመችስ  ናቸው። በአሁኑ ወቅት የተቀነባበረ የሽንኩርትና የቲማትም ምርት በኢትዮጵያ አየር መንገድ  በኩል ወደ ውጭ ለመላክ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ የሚገኙ ከ70 በላይ የህብረት ሥራ ዩኒዬኖች ከ7ሺህ 990 በላይ መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት በአባልነት ያቀፉ ሲሆን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም