የሰላም ጥሪያቸውን ሁሉም እንዲቀበላቸው ሴት የሰላም አምባሳደሮች ጥሪ አቀረቡ

85
መቀሌ ህዳር 18/2011 መከፋፈልን በማስቆም ሰላም እንዲሰፍን እያቀረቡ ያሉትን ጥሪ ሁሉም እንዲቀበላቸው ሴት የሰላም አምባሳዶሮች ጥሪ አቀረቡ። ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 22 ሴት አምባሳደሮች ከትግራይ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተወያይተዋል። ሴት አምባሳደሮቹ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ከሀገሪቱ  ህዝብ ግማሽ የሆኑት  የሴቶችን የሰላም ጥሪ ኃላፊነት ተሸክመው በየክልሉ  ስለሰላም መዘመር ጀምረዋል። መከፋፈል አብቅቶ የሀገሪቱ ልጆች አንድ  ሆነው በጋራና  በእኩልነት የሚኖርባት ኢትዮጵያን እንደሚሹ ተናግረዋል፡፡ የሰላም እጦት ሲፈጠር የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ ሴቶችና ህጻናት በመሆናቸው ልጆቻቸው ህልውና ሲሉ ስለ ሰላም እየሰበኩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከድሬዳዋ አስተዳደር የተወከሉት አምባሳደር ወይዘሮ ዛህራ ዑሶ በሰጡት አስተያየት "ዘርን መሰረት ያደረገ ጥላቻ እንዲቆም እንፈልጋለን " ብለዋል። መከፋፈልን በማስቆም  ሰላም እንዲሰፍን በየክልሉ በመዞር እየለመኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሀረሪ ክልል የተወከሉ አምባሳደር ወይዘሮ ገነት አሰፋ  "እኛ አምባሳደሮች የ50 ሚሊዮን እናቶች ጥያቄ በመቀበል በየክልሉና ከተማ አስተዳደሮች እየዞርን ነው" ብለዋል። የሰላም ጥሪያቸውን  ሁሉም እንዲቀበላቸውም  ሴት የሰላም አምባሳደሮቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል  በበኩላቸው የክልሉ ህዝብ ለሰላም ከፍተኛ መስዋእትነት መክፈሉን ገልጸዋል፡፡ ሰላሙ እንዳይበጠበጥ በከፍተኛ ኃላፊነትና ማስተዋል በተሞላበት መጠበቁን አመልክተው የሴት የሰላም አምባሳደሮቹ ተልዕኮ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "ከጎናችሁም እንቆማለን፤ ዋና መልዕክታችሁ ግን ሰላም የተጣበት ክልል ሰላም እንዲያስፍን ጥሪያችሁን ማቅረብ አለባችሁ "ብለዋል። የፌደራል መንግስትም በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን ግዴታውን እንዲወጣ ሴት አምበሳደሮች የድርቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ በክልሉ ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ የኢትዮጵያ ልጆች የትግራይ ህዝብ በክብር ተቀብሎ እንደልጆቹ በስርዓት እያስተናገዳቸው መሆኑን ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል። የሰላም አምባሳደሮቹ ከክልሉ ካቢኔ አባላት፣ከአፈ ጉባኤው እና ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር እንደሚወያዩ ተገልጸዋል። ከሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በመዘዋወር የሰላም ጥሪያቸውን እንደሚያቀርቡ የሰላም አምባሳደሮቹ አስተባባሪ ወይዘሮ  ገነት አሰፋ አስታውቀዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም