"የርእዮተ ዓለም ልዩነት የጋራ ኃብት እንጂ የልዩነት መነሻ መሆን የለበትም"- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

86
አዲስ አበባ ህዳር 18/2011 "የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ልዩነት የአገር የጋራ ኃብት እንጂ የልዩነት መነሻ መሆን የለበትም" አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ዛሬ በጀመሩት ውይይት ላይ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ንግግራቸው ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት እየተካሄደ ባለው በዚሁ ውይይት ላይ ቁጥራቸው ከ81 በላይ የሆኑ በአገር ውስጥ የተመዘገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው ከውጭ አገር የተመለሱ ፓርቲዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው። ውይይቱ መጪውን ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ማድረግ እንዲቻል ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የማሻሻያ ስራዎችና የጋራ ኃላፊነት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት የመወያያ መነሻ ሀሳብ እንዳሉት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርስ በመወያየት እና በአገር ጉዳይ ላይ በመሳተፍ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥም የውይይቱ ዓላማ ነው ብለዋል። በመጪው ዓመት በሚጠበቀው አገር አቀፍ ምርጫ የሚኖረውን የጨዋታ ህግ  ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ማዘጋጀት፤ ለሚመጣው ውጤትም በጋራ ተገዢ መሆን አስፈላጊነትንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ጠቁመዋል። "ፓርቲዎች የአገሪቱን ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ እንደ መርህ ተገንዝበውና ተረድተው መነሳት ይገባቸዋል፤ የኋላ የቁርሾ ታሪኮችን ከመቀስቀስ ልንቆጠብ ይገባልም" ነው ያሉት። የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ልዩነት የአገር የጋራ ኃብት አድርጎ መመልከት እንጂ የልዩነት መነሻ ሆኖ መቅረብ አንደሌለበትም አሳስበዋል። በተጨማሪም "የፖለቲካ ፓርቲዎች ከወከልነው ህዝብና ከመጣንበት ክልል ባሻገር እንደ አገር ለህዝብ መቆም እና ብዝሃነትን መቀበል ይገባል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ህገ መንግስቱን እና በሥራ ላይ ያሉ ህጎችን ማክበር እንዲሁ ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል። የዛሬው ውይይት ከግጭት የጸዳ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደሚረዳም  ጭምር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም