በሞያሌ በኩል ወደ ሀገር የገባ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዘ

1741

አዳማ ህዳር 18/2011 ከሀዋሳ ወደ አዲስ አባባ በከባድ ተሽከርካሪ ከነተሳቢው ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረ የኮንትሮባንድ ዕቃ ሞጆ ከተማ አቅራቢያ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

እቃው በሞያሌ በኩል ከውጭ የገባ ነው፡፡

በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ፈጥኖ ደራሽ ምስራቅ ዲቪዥን ሻለቃ ሁለት የሎጂስቲክ ኃላፊ ኢንስፔክተር ጀሞ ጋረደው እንደገለጹት የኮንትሮባንድ ዕቃው የተያዘው ህዳር 15/2011ዓ.ም.  ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ነው፡፡

ሞጆ ከተማ አጠገብ  ዲቦራ በተባለው አካባቢ በህብረተሰቡ ጥቆማ የተያዘው የኮንትሮባንድ ዕቃው የታርጋ ቁጥሩ  ኮድ 3- 83285 ኢት በሆኑ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ከነተሳቢው እንደተጫነ መሆኑን አስረድተዋል። 

በገቢዎች  ሚኒስቴር የአዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የህግ ማስከበር የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ብርሃኑ ለታ በበኩላቸው ዕቃውን ከተሽከርካሪው አራግፎ ለመቁጠር ሁለት ቀናት እንደወሰደ ገልጸዋል፡፡

በቆጠራው መሰረት 222 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅና 7 ቦንዳ አዳዲስ  የሴት አልባሳት መገኘቱን አመልክተው ዋጋውም ከ509 ሺህ ብር በላይ  እንደሚገምት አስታውቀዋል፡፡

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከሚያስከትለው  አፍራሽ ተፅዕኖ  ባሻገር በተለይ ልባሽ ጨርቆች  ፣ መድሃኒቶች፣ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች በህብረተሰቡ ጤንነት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትሉ በመከላከሉ ሂደት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢስፔክተር ጀሞ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።