ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በመጪው ሳምንት በሐዋሳ ከተማ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በመጪው ሳምንት በሐዋሳ ከተማ ይከበራል
64
አዲስ አበባ ህዳር 18/2011 ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በመጪው ሳምንት በሐዋሳ ከተማ እንደሚከበር የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም ለ27ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ለ26ኛ ጊዜ " አካል ጉዳተኞችን በማብቃት አካታችነትና እኩልነትን እናረጋግጥ " በሚል መሪ ሐሳብ ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ይከበራል፡፡ በበዓሉ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ይገኛሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከመሪ ሐሳቡ ለመገንዘብ እንደሚቻለው የከተማ አቀማመጥ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እናደርጋለን፤ ውብና ፅዱ የሆነ ከተማ እናያለን የሚሉ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ያለመ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት / ዩኤን/ "በ2030 ዘላቂ የልማት ግቦች እናሳካለን የሚለውን ከግብ ለማድረስ እንረባረባለን የሚለውን እንደ መሪ ሐሳቡ መምረጡን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በቃሉ መሠረት በከተማ ደረጃ በጣት ከሚቆጠሩ ከተሞች መካከል በግንባር ቀደም ፅዱና ውብ በሆነችው ሀዋሳ ከተማ በዓሉን ለማክበር መርጠናል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፡፡ የበዓሉ ዋና ዓላማም መሪ ሐሳቡን ለመንግሥት ተቋማት፣ ለአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ለሲቪል ማህበረሰብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው ፡፡ ፌዴሬሽኑ ያስቀመጣቸው ግቦችና ለአካል ጉዳተኛ የወጣውን የህንፃ አዋጅ ለማሳካትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በአገሪቱ የሚገነቡ ህንፃዎች፣ ሆቴሎች ፣ባንኮች ሆስፒታሎችና የንግድ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ በሚሉና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፣ ከሲቪል ማህበራት፣ ከመላው አገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ አደረጃጀቶች የተውጣጡና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥትና፣ የክልል አካላት ይሳተፋሉም ተብሏል፡፡