የኢትዮጵያና ቻይና የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዝ ኮንፍረንስ ተካሄደ

56
ጎንደር ህዳር 17/2011 የኢትዮጵያና ቻይና ሁለንተናዊ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያግዝ አለም አቀፍ ኮንፍረንስ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ተካሄደ፡፡ በዩኒቨርስቲው የህግ ትምህርት ቤት አዘጋጅነት በቻይና-አፍሪካ የውጭ ንግድና ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ዙሪያ በህግና ፖሊሲ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶችና የተዋናይ አካላት ሚና በሚል ርዕስ ነው ኮንፍረንሱ ዛሬ የተካሄደው፡፡ የኮንፈረንሱ አስተባባሪና የዩኒቨርስቲው የህግ መምህር  ዶክተር ሰሎሞን ተክሌ እንደገለጹት የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ለማገዝ  ነው፡፡ " ኢትዮጵያ ያላት ምቹ  ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ አንዱና ዋነኛው ነው"  ያሉት ዶክተር ሰሎሞን ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀመም በቀጣይ ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያና ቻይና በንግድና ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ አስተዳደርም በጋራ መስራት የሚችሉበት እድሎች እንዲሁ፡፡ ዶክተር ሰሎሞን  እንዳሉት ሀገሪቱ ያላት ፈጣን የመሰረተ ልማት ግንባታ  ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ጥሬ እቃ ለማስገባት፣ ከተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ጋር አባልና ለኢንቨስትመንት ተስማሚ የአየር ንብረት ባለቤት መሆኗ በዘርፉ ውጤታማ ያድርጋታል፡፡ "በኢትዮጵያ ከፍተኛ  የማዕድንና ኢነርጂ ሀብት፣ ገበያ ተኮር የሆኑና ለኢንዱስትሪ በቀጥታ የሚውሉ የግብርና ምርቶች የሚመረቱባት ፣  ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖራት የንግድና ኢንቨስትመንት ቁርኝት ሁለቱም ሀገሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ "ያሉት ደግሞ አለም አቀፍ የልህቀት ማዕከል አማካሪው  አቶ ጌድዮን ጃላታ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር መሳይ ሙሉጌታ በኢትዮ ቻይና ግንኙነት ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትና ንግድ ዘርፍ ያሉ አዝማሚያዎች፣ ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች በሚል ርዕስ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ በዚሁ ጽሁፋቸው ኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ የትብብር ዘርፎ ከ60 በላይ ስምምነቶች መፈራረማቸውን አመልክተው አንድ ሺህ 171 የቻይና ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ቀጣይ ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ ለማድረግም አነስተኛ የሆነ ብድር፣ የእዳ ስረዛ፣ ካባቢ አየር ጋር የተስማሚ ኢንቨስትመንት፣ የአካባቢው ህብረተሰብ የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጥራት ያላቸው ምርቶችና አገልግሎት እንዲሁም በመስና መከላከል ዙሪያ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በኮንፈረንሱ በቻይና-አፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ተግዳሮቶች ዙሪያ ንግግር ያደረጉት የዣንግ ጎንግ ሻንግ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ዩ ያኒንግ  አሁን በሀገሪቱ  ያለው የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታ ቀጣይ ቻይና በኢትዮጵያ ለሚኖራት የንግድና የኢንቨስትመንት ማሳደግ ስራ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ለአንድ ቀን በተካሄደው ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የህግ ትምህርት ቤት ተወካዮች፣ የመንግስት ስራ ኃላፊዎችና ከቻይና የህግና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም