ንቅናቄው በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትን በማጥራት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገለጸ

69
ጋምቤላ  ህዳር 17/2011 የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ ጋህአዴን / በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትን በማጥራት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ። የክልሉ አመራር አካላት በጋምቤላ ከተማ ለሁለት ሳምንታት ያካሂዱትን ግምገማ 14 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ዛሬ አጠናቀዋል። የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ወቅት እንዳሳሰቡት በሁሉም እርከኖች በሚገኙ የአመራር አካላት ሙስና፣ ብልሹ አሰራሮችና የአመለካከት ችግሮችን ለማጥራት መሥራት ይገባቸዋል። ድርጅቱ በማዕከላዊ ኮሚቴው የጀመረውን ጥልቅ ግምገማ ከክልል እስከ ወረዳ በሚገኙ የአመራር አባላት ላይ ማካሄዱን ተናግረዋል። ግምገማው በሙስናና በብልሹ አሰራር የተዘፈቁና የሥነ- ምግባር ጉድለት ያሳዩ 11 አመራር አባላትን ከድርጅቱ ማሰናበቱን ገልጸዋል። በሌሎች አመራሮች ላይም የስድስት ወር ክትትል እንደዲደረግባቸውና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የተጀመረውን ጥልቅ ግምገማ እስከ ቀበሌ በማዝለቅ  በችግሩ የተዘፈቁ አመራር አባላትን እንደሚያጠራ ሊቀመንበሩ አመልክተዋል። የክልሉን ሰላም በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማስቀጠልም ጥረቱ ይቀጥላል ብለዋል። የግምገማው ተሳታፊዎች ባወጡት የአቋም መግለጫ በክልሉ የሚታዩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት ችግሮችን ለመፍታትና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። በክልሉ  ከገጠርና ከከተማ መሬት፣ከፕሮጀክቶች፣ ከመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚታዩ የሙስናና ብልሹ አሰራሮች ችግሮችን እንደሚታገሉ አመልተዋል። የክልሉን የገቢ አቅም በማሳደግ የልማት ሥራዎችን የማፋጠንና አገራዊ  ለውጡን ለማራመድ መዘጋጀታቸውንም በአቋም መግለጫቸው ገልጸዋል። በሥራ ዕድል ፈጠራ የወጣቶችና የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩም ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል። የድርጅቱ የውስጥ ዴሞክራሲያዊ ትግል ለማዳበር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። ከህዳር 5 ቀን ጀምሮ በተካሄደው ጥልቅ ግምገማ ከ550 የአመራር አባላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም