በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የተጠያቂነት አሰራር መዘርጋት አለበት

94
አዲስ አበባ ህዳር 17/2011 በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ዘመናዊና የተጠያቂነት አሰራርን መዘርጋት እንዳለበት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር አስታወቀ። ማህበሩ በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለማስወገድ የእውቀት ሽግግር የሚካሄድበት መድረክ ዛሬ አዘጋጅቷል። በመድረኩ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ እንዳሉት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማፋጠን መንግስት "በሰዎች ዝናና ስም የሚለኩ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም" ሁኔታ መለወጥ አለበት። ፕሮጀክቶች በትክክል በተፈጸሙት ስራ ልክ ተገምግመው የተሻለ አፈጻጻም ያላቸው ባለሙያዎች የዕውቀት ሽግግር እንዲኖርና በአግባቡ ያልፈጸሙትን ደግሞ ተጠያቂ የማድረግ ስራ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት ይላሉ። የአገሪቷ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ባለፉት 10 ዓመታት ተከታታይ እድገት ያስመዘገበ ቢሆንም ኢኮኖሚውን የመደገፍ አቅሙን ለመጨመር ከተጠያቂነት ባሻገር ዘመናዊ አሰራርና የባለሙያውን አቅም መጨመር ላይ መሰራት አለበት ብለዋል። በዘርፉ የሚታየውን የጥራት፣ የጊዜ፣ የዲዛይንና የሰው ሃይል ችግር ለመፍታትና የታዳጊ አገራትን ተሞክሮ መቀመር ጠቃሚ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ካሊድ አብዱራህማን በበኩላቸው መንግስት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እያሳየ ያለውን እድገት ለማጠናከር በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል። የኮንስትራክሽን ፖሊስው በ2006 ጸድቆ ወደ ስራ መገባቱንና በ2009 በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የኮንስትራክሽን ምክር ቤት መቋቋሙንም ጠቁመዋል። በ2025 አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ ለመፍጠር ከአቅም ግንባታና ከቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከባላድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል። በተለይ ከጥራትና ከዋጋ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር እያከናወነ ያለውን ስራ ለማጠናከር የዛሬው ውይይት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል። የአገሪቷ የኮንሰትራክሽን ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚውን የመደገፍ አቅሙ እ.አ.አ በ2016 በ9 ነጥብ 6 ማደጉን የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም