ለ24 ሰዓታት በዛፍ ላይ የቆየው ግለሰብ በሰላም ወረደ

2233

ደብረማርቆስ  ህዳር 17/2011 በደብረ ማርቆስ ከተማ ረጅም ዛፍ ላይ ወጥቶ ” አልወርድም” ያለው ግለሰብ ከ24 ሰዓት ቆይታ በኋላ ጉዳት ሳይደርስበት መውረዱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በከተማው ቀበሌ ሶስት በሚገኘው 30 ሜትር ያህል ርዝመት ባለው ዛፍ ከትናንት ጀምሮ ወጥቶ የቆየው ይሄው ግለሰብ ሊወርድ የቻለው ከብዙ ማግባባት በኋላ ነው፡፡

በከተማው አስተዳደር የአንደኛፖሊስ ጣቢያ ጽህፈት ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና የስራሂደት ባለቤት ኮማንደር  ለገሰ አባተ እንዳሉት በዛፉ ላይ ለ24 ሰዓታት የቆየው ግለሰቡ ሌሊት ጉዳት እንዳይደርስበት ፖሊስ ጥበቃ ሲያደርግ አድሯል፡፡

በትዕግስት በተደረገ ማግባባት ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ከዛፉ ላይ በሰላም ሊወርድ ችሏል።

ግለሰቡ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ከዛፍ ሊወጣና አልወርድም ያለበትን  ምክንያት በውል እንደማያውቅ ተናግሯል።

በደብረማቆስ ከተማ  ለዘጠኝ ዓመታት ጫማ በመጥራግና በቀን ስራ ሲተዳደር መቆየቱን ገልጿል፡፡

ሆኖም የእጅ መንቀጥቀጥ ችግርና የአካል ጉዳተኛ በመሆኑ በሚፈለገው ልክ ሰርቶ እራሱን መቻል አቅቶት ይጨነቅ እንደነበረም ጠቁሟል፡፡

ድጋፍ ከማጣትና በኑሮ አለመሟላት ምክንያት የአእምሮ ጭንቀት እንዳለበትና ድርጊቱንም እንደማያስታውሰው አመልክቷል።

የግለሰቡን ችግር በመረዳት ከማህበረሰቡ ድጋፍ አሰባስበው  ለማገዝ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ኮማንደር  ለገሰ አመልክተው ችግሩን ለማቃለል የከንቲባው ጽህፈት ቤት የመኖሪያ ቤት እንዲያመቻችለት እየተነጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግለሰቡ  ከትናንት  ጀምሮ  ዛፍ ላይ ተሰቅሎ “አልወርድም”  ብሎ እንደቆየ ቀደም ብሎ ኢዜአ  ዘግቧል፡፡