በሙስና ሊመዘበር የነበረን ከ97 ሚሊዮን በላይ ብር ማዳን ተቻለ

105
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2010 በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራ ከ97 ሚሊዮን  ብር በላይ ማዳኑን አገር አቀፍ የጸረ-ሙስና ጥምረት ስራ አስፈጻሚ አስታወቀ። ጥምረቱ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም ባደረገው የሁለት ዓመት የሙስና ቅድመ መከላከል ስራ ሊመዘበር የነበረ የህዝብና የመንግስት ገንዘብ ማዳኑን ገልጿል። ጥምረቱ በ2008 እና በ2009 ዓም ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። የጥምረቱ ስራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲሃ የሱፍ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስርሜሽን ዕቅድ ሙስናን መከላከልና ከምንጩ ማድረቅ ትኩረት ከተሰጠባቸው ተግባራት አንዱ ነው። ከዚህ አንጻር ሙስና በአገር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመረዳትና ሁሉን ያሳተፈ ትግል እንዲካሄድ በማወጅ የጸረ-ሙስና ትግሉን የሚመሩና የሚያስተባብሩ የስነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ ተደርጓል ብለዋል። በዚህም ጥምረቱ ባካሄደው አስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራ በህዝብና መንግስት ላይ ሊደርስ የነበረውን 97 ሚሊዮን 961 ሺህ 971 ብር ከኪሳራ መከላከል ተችሏል ነው ያሉት። ገንዘቡ ያለአግባብ በሚወጡ ጨረታዎች፣ ግዥዎችና በሌሎች የሙስና ተግባራት ሊመዘበር የነበረ መሆኑን ጠቁመዋል። ከህብረተሰቡ በሚደርሱ ጥቆማዎችና ጥምረቱ በሚያካሂደው የሙስና መከላከል ስራ ምዝበራውን መታደግ መቻሉን ነው ወይዘሮ ፈቲሃ  ያስረዱት። በተጨማሪም የ110 ሺህ 139 የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞችን የሃብት ምዝገባ ተግባር መከናወኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል። እንዲሁም በተመረጡ 106 የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ተቋማት፣ በኃይል ማመንጫ፣ በስኳርና የመስኖ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ በሰባት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ጥናት በማካሄድ ለሙስና ያልተመቸ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት። የፌደራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽነር አየልኝ ሙለዓለም በበኩላቸው ጥምረቱ ሙስናን በተቀናጀ መልኩ በጽናት በመዋጋትና መልካም ስነ-ምግባርን በማስፋት ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ብለዋል። ኮሚሽኑ የጥምረቱን ዕቅድ አፈጻጸም በመከታተል የተለያዩ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናና ልምድ ልውውጥ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በቀጣይም የጸረ-ሙስና ጥምረት ስራ አስፈጻሚ በሚያደርጋቸው የሙስና መከላከል ተግባራት ላይ ኮሚሽኑ በበላይነት በመምራትና በማስተባበር ሙስናን ለመከላከል እንደሚሰራ አመልክተዋል። የጸረ-ሙስና ጥምረቶች የሙስና ተሳታፊዎችንና ፈጻሚዎችን በማጋለጥ ተጠያቂ ማድረግ መጀመራቸው ጥሩ ጅምር ቢሆንም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውና ህብረተሰቡም በዚህ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆን አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም