በሙስና እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

66
አዲስ አበባ ህዳር 17/2011 በሙስና እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩ ከ60 በላይ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ። በብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲ እና በጎሃ አጽብሃ መዝገብ የተካተቱ ተጠርጣሪዎች ናቸው ዛሬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት። በተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ተጠርጣሪ የዶክተር ሀሽም ቶፊቅ ባለቤት ዊዳት አህመድን ጨምሮ ሌሎች አራት ግለሰቦች የሙስና ወንጀልና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎችና ማስረጃ በማሸሽ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ተጠርጣሪዎቹ አንደኛ ፊልሞን ግርማይ፣ ሁለተኛ ቴዎድሮስ ጣዕምአለው፣ ሶስተኛ ወይዘሮ ዊዳት አህመድ እና አራተኛ ሰሚራ አህመድ ናቸው። ፊልሞን ግርማይና ቴዎድሮስ ጣዕምአለው የተባሉት ተጠርጣሪዎች የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የአንድ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ገብረጻዲቅ በተጠረጠሩበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈለጉ እያወቁ የጦር መሳሪያዎችና ሰነዶችን በመደበቅና በመሸሸግ መተባበራቸውን ፖሊስ ከመድረሱ በፊት በመሰወርና በማጥፋት መጠርጠራቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል። ሶስተኛና አራተኛ ተጠርጣሪ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ተጠርጣሪውን ዶክተር ሃሽም ቶፊቅን በማሸሽና ሰነድ በማጥፋት፤ እንዲሁም ከሁለት ሽጉጦች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዛቸውንና ቤት ተመልሰው ሰነድ ማጥፋታቸውን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል። ፍርድ ቤቱ በዛሬ ውሎው አንደኛና ሁለተኛ ተጠርጣሪ በዋስ ቢወጡ ተቃውሞ እንደሌለው አስረድቷል፤ በ10 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁም ችሎቱ ወስኗል፤ ሶስትና አራተኛ ተጠርጣሪዎች ግን በቤተ ዘመድና ቤተሰብ ስም ያለአግባብ ሃብት በማካበት ስለተጠረጠሩ ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም