ኢትዮ-ቴሌኮም የኤሌክትሪክ ኃይልን ፋይበር ኦፕቲክ ለመጠቀም ተስማማ

140
አዲስ አበባ ህዳር17/2011 ኢትዮ-ቴሌኮም በኤሌክትሪክ መስመር ፋይበር ኦፕቲክ መጠቀም የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተፈራረመ። በስምምነቱ መሰረት ቴሌኮሙ 3 ሺህ 283 ኪሎ ሜትር ለሚሸፍነው የመስመር አገልግሎት በዓመት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ለኤሌክትሪክ ኃይል ይከፍላል። ኢትዮ-ቴሌኮም ላለፉት ሰባት ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል በዘረጋው ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ የሚገኘውን አራተኛ ገመድ /ፋይበር ኦፕቲክስ/ ያለ ተቋሙ ፈቃድ ሲጠቀም ምንም አይነት ክፍያ አልፈጸመም። የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እና የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ናቸው ስምምነቱን የተፈራረሙት። ወይዘሪት ፍሬህይወት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት መስመሩን በስምምነት ለመጠቀም ድርድሮች ሲደረጉ ቆይተዋል። በተደረሰው ስምምነትም ቴሌኮሙ ላለፉት ሰባት ዓመታት የተጠቀመበትን የአገልግሎት ክፍያ ይፈጽማል፣ በቀጣይም በየዓመቱ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ለመክፈል ተስማምቷል። የቴሌኮሙ ከመሬት በላይ በተዘረጋው መስመር መጠቀም በመሬት ውስጥ የዘረጋቸው የኔትወርክ መስመሮች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ብልሽት ሲገጥማቸው የኔትወርክ መቆራረጥ እንዳይኖር እንደሚያግዝ ተናግረዋል። መስመሩ ከፍተኛ ዳታ የመሸከም አቅም ያለው በመሆኑም 'የቴሌኮም አገልግሎቱን የተሻለ ያደርገዋል' ነው ያሉት። ወጪው በመሬት ውስጥ ለተዘረጋው መስመር ጥገና ከሚወጣው ያነሰ እንደሆነም አክለዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው እንዳሉት መስመሩ ከኃይል ማስተላለፊያነት በተጨማሪ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል በመሆኑ የአገርን ሃብት በቅንጅት መጠቀም ያስችላል። ቴሌኮሙ ያለተቋሙ ፈቃድ መጠቀሙ ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር አስታውሰው በቀጣይ በጋራ ለመጠቀም መስማማታቸውን ገልጸዋል። ይህ አንድ ገመድ በውስጡ 6 ጥንድ የፋይበር መስመሮች ያሉት ሲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከእነዚህ መካከል አንዱን ብቻ ነው የሚጠቀመው። ኢትዮ-ቴሌኮም ከአዲስ አበባ ጅማ፣ ጋላፊ፣ ደሴ፣ መቀሌ፣ አምቦ፣ ጌዶ፣ መቱ፣ ጋምቤላ፣ አዋሽ፣ ባህርዳርና መተማ ያለውን 3 ሺህ 283 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን መስመር በኪሎ ሜትር 1 ሺህ 035 ብር ለመክፈል ነው ስምምነት የፈረመው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም