በደብረማርቆስ ከተማ አንድ ግለሰብ ከትናንት ጀምሮ ዛፍ ላይ ወጥቶ አልወርድም አለ

61
ደብረማርቆስ ህዳር 17/2011 በደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር አንድ ግለሰብ ትናንት ከሰዓት ጀምሮ ረጅም ዛፍ ላይ ተሰቅሎ አልወርድም ማለቱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በአስተዳደሩ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ጽህፈት ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር ለገሰ አባተ ለኢዜአ እንዳሉት ግለሰቡ በዛፍ ላይ ተሰቅሎ የሚገኘው በከተማዋ ቀበሌ ሶስት ውስጥ ነው፡፡ ከ30ሜትር በላይ ከፍታ ባለው ዛፍ ላይ የተሰቀለው ግለሰቡ እንዲወርድ የማግባባት ስራ ቢከናወንም ፈቃደኛ ሳይሆን እስካሁን ባለበት እንደሚገኝ አመልክተዋል። "ግለሰቡ በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚሆን ይገመታል" ያሉት  ኮማንደሩ ለማነጋገር ሲሞከር መልስ እንደማይሰጥና ማህበረሰቡም ሆነ የፖሊስ አባላት ለማውረድ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ለማወረድ ጥረት በሚደረግበት በአሁኑ ወቅት ወደላይ በሚወጣበት የዛፉን ቅርንጫፎችን እየሰባበረ ለመማታት በመሞከር ማስቸገሩን ገልጸዋል። ከትናንት ጀምሮ ሌሊቱን ሙሉ ፖሊስ ጥበቃ ሲያደርግ ማደሩን ጠቁመው፤ ማህበረሰቡ ከፖሊስ ጋር በመተባበር የማግባባት ስራው መቀጠሉን  አስታውቀዋል። ግለሰቡ በቅፅል ስሙ ቄሴ እየተባለ የሚጠራና በደብረማርቆስ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አካባቢ ጫማ በመጥረግ ስራ የተሰማራ እንደነበር በቅርበት እንደሚያውቁ  የአካባቢ ነዋሪዎች እንደገለጹላቸው ኮማንደሩ አመልክተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በቦታው እንዳልነበርና አይተውት እንደማያውቁ ነዋሪዎቹ እንደነገሯቸውም ጠቁመዋል፡፡ የግለሰቡን ቤተሰብ የማፈላለግ ስራ እየተካሄደ መሆኑንና ማህበራዊ ሁኔታውን ለማወቅ ፖሊስ እያጣራ እንደሚገኝም አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅትም የፀጥታ አካላትና የአካባቢው ማህበረሰብ ዙሪያውን ከቦ እየጠበቀው እንደሚገኝም ኮማንደር ለገሰ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም