በነቀምቴ ከተማ በ60 ሚሊዮን ብር የሪፈራል ላቦራቶሪ ማስፋፊያ ግንባታ እየተካሄደ ነው

97
ነቀምቴ ግንቦት 16/2010 በነቀምቴ ከተማ በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የሪፈራል ላቦራቶሪና የሕብረተሰብ ጤና ምርምር ማዕከል የማስፋፍያ ግንባታ እየተካሄደ ነው። በኦሮሚያ ጤና ቢሮ የነቀምቴ ሪፈራል ላቦራቶሪ እና የሕብረተሰብ ጤና ምርምር ማዕከል ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሶሪ እንደተናገሩት የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ እየተከናወነለት ያለው ማዕከል ለስምንት የምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ማዕከሉ በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ 13 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተዋል። አቶ ጌታቸው እንዳሉት፣ የማስፋፊያ ግንባታው ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ ሲሆን፣ የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ ወደስራ ሲገባ በኦሮሚያ ከልል ቀደም ብለው የተገነቡ ዘመናዊ ሪፈራል ላቦራቶሪዎችን ቁጥር ወደአምስት ያሳድገዋል። ቤተሙከራው በምዕራብ ኦሮሚያ ከሚገኙ ስምንት ዞኖች የተለያዩ የጤና ተቋማት የሚላኩ የደም ናሙናዎችን ለመመርመር የሚያስችል ሲሆን ውጤቱን በፍጥነት ለማሳወቅ የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችም እንደሚገጠሙለት አቶ ጌታቸው አመልክተዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ያሬድ ጉተማ በበኩላቸው የማዕከሉ ግንባታ "ሲዲሲ ኢትዮጵያ" ከተባለ ግብረሰናይ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ በ2008 ዓ.ም መጀመሩንና በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ መገባደዱን ገልጸዋል። በማስፋፊያ ሥራው እየተገነባ ያለው ባለአንድ ፎቅ ሕንጻ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 58 ክፍሎች ያሉት ሲሆን በመጪው ዓመት መጀመሪያ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። የግንባታው ሥራ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሥራ አጥ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩንም ነው የገለጹት። የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ በኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ የተመረቀው ወጣት ቴዎድሮስ ግርማ በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር በትምህርት የቀሰመውን እውቀት በተግባር ለመፈፀም እንዳስቻለው ተናግሯል። ከተግባረዕድ ትምህርት ቤት በጄነራል ኮንስትራክሽን የተመረቀው ወጣት ሳሙኤል በበኩሉ "በላቦራቶሪው ግንባታ መሳተፌ በአንድ በኩል ሰርቶ ገቢ ለማግኘት በሌላ በኩል ተጨማሪ ልምድና እውቀት ለመቅሰም እየጠቀመኝ" ነው ብሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም