የመልካ ሶር እሬቻ በዓል በኢሉአባቦር ዞን በድምቀት ተከበረ

79
መቱ  ህዳር 16/2011 በኢሉአባቦር ዞን የመልካ ሶር እሬቻ በዓል ዛሬ በድምቀት ተከበረ፡፡ በበአሉ ላይ ከኢሉአባቦር ዞን የተለያዩ ወረዳዎችና አጎራባች የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የመጣ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታድመዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የሰግለን ኢሉ አባገዳ ከሊፋ ሾኖ ባሰሙት ንግግር የኦሮሞ ህዝብ በየአመቱ የሚያከብረው እሬቻ በዓል አካል የሆነው የመልካ ሶር እሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪን ለማመስገንና ፍቅርን ለመግለጽ የሚያከብረው ባህላዊ ስነስርአት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚታየውን ሰላምና መረጋጋት በመጠበቅ ለባህልና ማንነታቸው መጎልበት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ "የገዳ ስርአት አስተምህሮት ለአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ትልቅ ትኩረት ይሰጣል” ያሉት አባገዳው ህብረተሰቡም በዓሉን ሲያከብር ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት በመስጠት መሆን አንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የመቱ አባገዳ ተሰማ ሙሉነህ በበኩላቸው እንዳሉት የመልካ ሶር እሬቻ በዓል የሚከበርበት አካባቢን የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ ከመቱ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ጋር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በዘንድሮው በዓል ላይ ካለፉት ዓመታት አንጻር በርካታ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመቱ ከተማ ቀበሌ 03 የሚኖረው ወጣት ኑሬ ጀማል እንዳለው የዘንድሮው የእሬቻ በዓል በሀገሪቱ ሁሉን ህዝቦች በአንድነት ያሰባሰበ ለውጥ በመጣበት ወቅት መከበሩ ልዩ ስሜት ፈጥሮለታል፡፡ በተለይ ባለፉት ቅርብ ዓመታት በጸጥታ ችግር የተነሳ ሁሉንም ህዝብ በማሳተፍ በድምቀት ለማክበር እንዳልተቻለ አስታውሶ ዘንድሮ ሁሉም በደስታና ሰላማዊ ሁኔታ በዓሉን በጋራ ወጥቶ ማክበሩን ተናግሯል፡፡ ከኦሮሞ ህዝብ የእሬቻ ክብረ በአላት አንዱ የሆነው የመልካ ሶር እሬቻ በዓል በየአመቱ በኢሉአባቦር ዞን መቱ ወረዳ ይከበራል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም