የኮትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል - የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አበቤ

138
ድሬዳዋ ህዳር 16/2011 የሀገሪቱን ፈጣን ልማት ለማደናቀፍና ሰላምን በማደፍረስ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየተፈጠረ የሚገኘውን የኮትሮባንድ እንቅስቃሴ ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡ የኮትሮባንድ እንቅስቃሴ እያሳደረ የሚገኘውን ሁለንተናዊ ተፅዕኖና በቀጣይ የመፍትሄ እርምጃዎች ዙሪያ የሚመክር ውይይት በድሬዳዋ ተጀምሯል፡፡ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዳሉት በሀገሪቱ የታክስ ስወራ፣ የኮትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ እንቅስቃሴዎች ህጋዊና ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዳይጎለብት እንቅፋት ሆነዋል፡፡ ለልማት መዋል ይችል የነበረውን በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ እንዳይሰበሰብ ከማድረግ በተጨማሪ  የውጭና የሀገር ውስጥ ንግድና ኢንቨስትመንትን እየጎዳው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ አቅም ማዳከሙን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የኮትሮባንድ ንግድ በፖለቲካው፣ በምጣኔ ሃብትና በማህበራዊ ዘርፍ እያሳደረ ከሚገኘው ተፅዕኖ ባለፈ ሰላምና ደህንነትን በማናጋት ለበርካታ ዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡ ይህን በሀገር ዕድገትና ሰላም ላይ መርዝ እየረጨ የሚገኘውን ኮትሮባንድ በተቀናጀ መንገድ መከላከልና በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የተሣተፉበት ውይይትም በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራትና የተደራጀ አሰራር ለመዘርጋት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው ኮትሮባንድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት የተዘረጋ ቢሆንም ችግሩን እንዲከላከሉ የተቋቋሙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚፈለገው መጠን አልተወጡም፡፡ በአሁን ሰዓት ወንጀሉ በረቀቀ መንገድ የነዳጅ ቦቴ ሣይቀር ለዚህ ሥራ እየዋለ እንደሚገኝ ገልፀው በሀገሪቱ ፀጥታ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚሁ የኮንትሮባንድ ንግድ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ጭምር በስፋት እየታየ መሆኑን ከንቲባ ኢብራሂም አስረድተዋል፡፡ ውይይቱ ሀገራዊ የለውጥ ጉዞው እንዳይደናቀፍ ችግሩን በተቀናጀ መንገድ በመከላከል ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ የሚረዳ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ እንደ ከንቲባ ኢብራሂም ገለጻ  ከፍተኛ ማነቆ የሆነውን  የኮትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ለመከላከል አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡ በውይይቱ  ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘውዴ ተፈራ የኮትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ችግሮች የመከላልና ቀጣይ አቅጫን ያመላከተ የውይይት ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ በፅፉአቸው ላይ ኮትሮባንድ በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብትና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ  መጠነ ሰፊ ችግር ማስከተሉን ተናግረዋል፡፡ በቀረበው ጽሁፍ ላይ እየተወያዩ የሚገኙት የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የፍትህና የፀጥታ ዘርፍ  አመራሮች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የገቢዎች ሚኒስቴር አመራሮች በቀጣይ የሚተገብሯቸውን ሥራዎች በውጤት ለመደምደም መግባባት ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም