ሀገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ወጣቶች ተናገሩ

54
ድሬዳዋ ኅዳር 16/2011 ህብረታቸውን በማጠናከርና የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ወጣቶች ተናገሩ፡፡ "በብዙሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ወጣቶቹ በሰላም ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች ለኢዜአ እንደገለጹት የዘመናት መገለጫቸው የሆኑትን ህብረትና ፍቅራቸውን አጽንተው የአካባቢያቸውን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ወጣት አዲል መሐመድ እንዳለው አመራሩ የራሱን  አንድነት ጠብቆ ወጣቱን በየጊዜው በሰላም ጉዳይ ላይ ማወያየት እንዳለበት ተናግሯል፡፡ "ባለፉት ጥቂት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጣው ለውጥ አስደሳችና ለወጣቱ ተስፋ የሰጠ በመሆኑ እኔም ሆንኩ ወጣቱ ይህን ለውጥ ከዳር ለማድረስ የድርሻችንን እንወጣለን" ብሏል፡፡ "በድሬዳዋ እየታየ የሚገኘው ሁከትና ብጥብጥ የኛ የድሬዳዋ መገለጫ አይደለም" ያለችው ደግሞ ወጣት አይናዲስ ኃይሌ ናት፡፡ መንግስት ለወጣቱ የሥራ እጥነት ችግር ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳለበት ገልጻ "የድሬዳዋ አመራሮች ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት እየሰጡ ያሉት ምላሽ ዝቅተኛ ነው" ብላለች፡፡ በድሬዳዋ የሚገኘው ወጣት በብሔር፣ በዘር፣ በሃይማኖት ሳይለያይ የቀድሞ አንድነቱን በመጠበቅ ለአካባቢውና ለሀገር ሰላም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት የገለጸቸው ደግሞ ወጣት ፎዚያ አሚን ናት፡፡ ወጣቱ ይህን ማድረግ ሲጀምር በሀገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥና ተስፋ ከፍጻሜ መድረስ እንደሚችልም ወጣቷ ጠቁማለች፡፡ ወጣት ሀምዛ አብደላ በበኩሉ ቀደም ሲል የድሬዳዋ ፖሊስ ችግር ከመከሰቱ በፊት በመረጃ ላይ የተደገፈ የመከላከል ሥራ ይሰራ እንደነበር አስታውሶ በቅርቡ እየተከሰተ ባለው ችግር ይህ ብቃቱ ባለመስተዋሉ ፖሊስ ራሱን እንዲገመግም ጠይቋል፡፡ "እየተፈጠረ ያለው ችግር በማንና እንዴት እንደሚከሰት ከወጣቱ የተደበቀ አይደለም" ያለው ወጣር ሀምዛ ከጸጥታ አካላት ጋር ሆነን ለሰላም መስራት አለብን " ብሏል፡፡ በድሬዳዋ የሳቢያን አካባቢ ወጣቶች አደረጃጀት ሰብሳቢ ወጣት ዮናስ ሀብታሙ በበኩሉ ወጣቱ በአካባቢው በሚፈጠር ችግር ተጎጂ መሆኑን ጠቁሞ በድሬዳዋ ነዋሪዎች መካከል ጥላቻን ለመፍጠር የሚደረገውን  ቅስቀሳ በጋራ በመመከት ሀገራዊ ለውጡን ከዳር ማድረስ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አብዱልሰላም መሐመድ በበኩላቸው ወጣቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን በመጠበቅ የአካባቢውን ሰላም በአስተማማኝ ደረጃ ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አስተዳደሩ የወጣቱን ዘርፈ-ብዙ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት  እየሰራ እንደሚገኝም አፈ-ጉባኤው አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በቀጣይ አስተዳደሩ ከሴቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር የውይይት መድረኮችን እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ በተያያዘ ዜና "ሳተናው" በሚል ስያሜ የተደራጁ የድሬዳዋ ወጣቶች ሰሞኑን በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ብጥብጥ ለተጎዱ ወገኖች ደም ለግሰዋል፡፡ በደም ልገሳ ፕሮግራሙም ከ60 በላይ ወጣቶች ሕይወት ለማዳን መሳተፋቸው ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም