ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ለውጡ ለማኑፋክቸሪንግ ግቡ ስኬት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል - ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

59
አዲስ አበባ ህዳር 16/2011 የተጀመረው ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ለውጥ ለማኑፋክቸሪንግ ግቡ ስኬት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ። ኢትዮጵያ በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር 2025 በአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል መሆን የሚያስችላት ለውጥ ላይ ትገኛለች ብሏል። አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር ለማሳለጥ በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ነው። የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ፍጹም አረጋ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የቀላል ማኑፋክቸሪንግ መዳረሻ ማድረግ የሚያስችል አቅም አለ። ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ እንደ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ኃይል፣ ህክምናና የምግብ ማቀነባበሪያ ያሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ምቹ ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል። መንግስት እያከናወነ ያለው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ለውጥ ለዚህ ግብ ስኬት ያለውን አዎንታዊ አስተዋፅኦም ገልጸዋል። የግብርና ምርቶች ኢንዱስትሪውን የሚመግቡ በመሆናቸው መንገድ ሲገነባና የኤሌክትሪክ መስመር ሲዘረጋ እነዚህን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነም አክለዋል። በቀጣይ የሚገነቡ የመሰረተ ልማተ አውታሮች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋትና ምቹ ማድረግ በሚያስችል መልኩ መሆን እንዳለባቸው "ትምህርት እያገኘን ነው" ብለዋል ኮሚሽነር ፍጹም። በመንግስት ደረጃ የሚታዩ የፖሊሲና የአሰራር ክፍተቶች "በተጀመረው ሪፎርም ምላሽ ያገኛሉ" ነው ያሉት። በተማረ የሰው ኃይልና በትንሽ መሬት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በማስፋፋት ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ቀጣይ የቤት ስራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም