የጣናን ሐይቅ ከእንቦጭ አረም ለመታደግ የኢትዮጵያዊያን ትብብር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

49
ባህርዳር ህዳር 15/2011 የጣናን ሐይቅ  ከተጋረጠበት የእንቦጭ አረም  አደጋ ለመታደግ የኢትዮጵያዊያን የትብብር ድጋፋ እንደሚያስፈልግ ከአዲስ አበባ  በስፍራው የተገኙ  በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ገለጹ። ወጣቶቹ የእንቦጭ አረም በሃይቁ ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ዛሬ ተመልክተዋል። የወጣቶች አስተባባሪ  ወጣት ብስራት ሙሉጌታ ለኢዜአ  እንዳለው ወደ ስፍራው  የመጡበት ዓላማ አንዱ  የባህርዳርና የአዲስ አበባ ወጣቶችን የእርስ በርስ ትስስርና አንድነት ለመፍጠር ነው፡፡ ሌላው " በጣና ሃይቅ ላይ የተጋረጠውን የእንቦጭ አረም ያለበትን ሁኔታ በአካል ተገኝተን በመመልከት ከተለያዩ አካላት ጋር በመነጋገር ወደ መፍትሄው ለመሄድ ነው "ብለዋል። ጣና የባህርዳር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሃብት በመሆኑ እነሱን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ  ወጣቶችና የሌላውም የህብረተሰብ ክፍል  የትብብር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡ አረሙን በእጅ ነቅሎ መጨረስ ስለማይቻል  በቀጣይ ወደመጡበት ሲመለሱ  ለማሽን መግዥ የሚሆን ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስተባባሪው ተናግሯል። " በአካል ተገኝቼ ሐቁን ስመለከት ጣና ከሚዲያ ከማየውና ከምሰማው በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ" ያለው ደግሞ  ወጣት አለማየሁ ወጉ ነው። የጣና ሃይቅ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በጋራ ተባብሮ ከተጋረጠበት አደጋ ሊታደገው እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ ችግሩን ለማያውቁ ወጣቶች በቀጣይ በማስረዳትም  ለእንቦጭ ማስወገጃ  መሳሪያ የሚገዛበት ገንዘብ ለማሰባሰብ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ  ተናግረዋል፡፡ ሌላው ወጣት አዲሱ በሰጠው አስተያየት በሃይቁ ላይ የተጋረውን አደጋ መጥተው መመልከት ላልቻሉ ጓደኞቹ እንደሚያስረዳ ተናግሯል። የእንቦጭ አረም እያደረሰ ያለውን ጥፋት በዘላቂነት ለመከላከልም ከሌሎች  የኢትዮጵያ ወጣቶች ጋር እንደሚሰራም ገልጿል። የጣና ቂርቆስ አንድነት ገዳም አስተዳዳሪ አባ ተክለስላሴ ወልደቂርቆስ በበኩላቸው በገዳሙ አካባቢ የእንቦጭ አረም የተከሰተው በ2004 ዓ.ም እንደሆነ ተናግረዋል። በአረሙ ምክንያት የገዳሙን የእርሻ መሬት በመወረሩ ላለፉት አራት ዓመታት ማምረት ማቆማቸውን አመልክተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ የመጡ ከ300 የሚበልጡ ወጣቶች ከባህርዳር አቻቸው ጋር ነገ በክልሉ ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሰላም ኮንፍረንስ እንደሚያካሄዱ ይጠበቃል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም