በሙስና የተከሰሱ 74 ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

94
ጎንደር ግንቦት 16/2010 በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የቆዩ 74 ግለሰቦች እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን በስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የጎንደር ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡ የቅርንጫፉ ኃላፊ አቶ ሰጥአርጌ መሰሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ቅርንጫፉ 240 የሙስና ጥቆማዎችን በመቀበል 142ቱ ትክክለኛ የሙስና ተግባር መሆናቸውን በማጣራት ክስ እንዲመሰረት አድርጓል፡፡ በአርባ አራት የክስ መዝገቦች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ከቆዩ የሙስና ተጠርጣሪ ግለሰቦች መካከል 74ቱ ጥፋተኛነታቸው በመረጋገጡ በእስራትና በገንዘብ ተቀጥተዋል፡፡ በእዚህም ግለሰቦቹ ከአራት ወር እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና አስከ 30 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን ነው ያስረዱት። የእስራት ቅጣት ከተላለፈባቸው ግለሰቦች መካከል በጎንደር ከተማ በጌጠኛ ድንጋይ ማንጠፍ ሥራ በማህበር የተደራጁ ወጣቶችን ገንዘብ ለግል ጥቅም ያዋሉ ሊቀ-መንበርና ጸሐፊ በ15 እና በ13 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመንግስት የሥራ ኃላፊነት ተቀጥረው ሲሰሩ የተገኙ አመራሮችና ግለሰቦችም አስከ ስድስት ዓመት በሚደርስ እስራት መቀጣታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ አቶ ሰጥአርጌ እንዳሉት ቅርንጫፉ ከሕዝብ በደረሰው የሙስና ጥቆማ መሰረት በግለሰቦች ተመዝብሮ ከነበረ የመንግስት ገንዘብ መካከል 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ማስመለስ ችሏል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ በተቀነባበረ ሴራ ከመንግስት ካዝና አላግባብ ወጥቶ ለግለሰቦች መጠቀሚያ ሊውል የነበረ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በመሬት ወረራ በግለሰቦችና በአመራሮች አላግባብ ተይዞ ከነበረ 4ሺህ ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ 2 ሺህ 620 ካሬ ሜትሩ ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ መደረጉንና ቀሪው መሬት ደግሞ በፍርድ ቤት እገዳ የተጣለበት መሆኑን አስረድተዋል። በሙስና ገንዘብ የተገዛ አንድ አይሱዚ የጭነት መኪናም በፍርድ ቤት ትእዛዝ በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉን ነው የገለጹት፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የሙስና ጥቆማ ቀርቦባቸው ማጣራት የተደረገባቸው 194 የሙስና ጥቆማዎች ጉዳያቸው በአቃቢ ህግና በፖሊስ በመመርመር ላይ እንደሚገኝም ኃላፊው አያይዘው ገልጸዋል፡፡ ቅርንጫፉ 1 ሺህ 191 የፖለቲካ ሹመኞችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ማድረጉ ታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም