መገናኛ ብዙሃን ከጥላቻና መለያየት ይልቅ በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ላይ መስራት አለባቸው

98
አዲስ አበባ  ህዳር15/2011 መገናኛ ብዙሃን  ከጥላቻና መለያየት ይልቅ በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። "ሚዲያ ለሰላም" በሚል አገር አቀፍ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አካላት የፓናል ውይይት  ዛሬ ተካሂዷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች መንግስት በህብረተሰቡ መካከል ጥላቻ የሚሰብኩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስራቸውን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አሳስበዋል። መገናኛ ብዙሃን በህዝቦች መካከል ግጭቶችን ከመፍጠርና ከማራራቅ ይልቅ አንድነትና መተባበርን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃን  እና  የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ማህበራዊ ሚዲያ እና መደበኛ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም በህዝቦች መካከል ግጭት የሚፈጥሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ መንግስት አስተማሪ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።  የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ እንዳሉት፤ መንግስት ግጭት የሚፈጥሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ አለበት።  መገናኛ ብዙሃን በዘርፉ ባለሙያ እንዲመራ፣ የስራ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ሊታሰብበት እንደሚገባ፣ መገናኛ ብዙሃን በፖለቲከኞች ጫና ስር መውደቅ እንደሌለባቸውም አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃን አካሄድ መሻሻል እንዳለበትና የህዝብ አጀንዳ መቅርጽ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።  በመድረኩ የተሳተፈው ወጣት ከድር አህመድ በበኩሉ መገናኛ ብዙሃን ግጭት ሳይከሰት እና ከተከሰተም በኋላ የመፍትሄ ሀሳብ በማቅረብ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ በግጭት አፈታት ላይ የሃይማኖት አባቶች እና አገር ሽማግሌዎች ከመንግስት ጋር ቢሰሩ መልካም መሆኑን ጠቁመዋል። ''መንግስት በሚፈጠሩ ግጭቶች ላይ ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ዳግም እንዳይከሰት መስራት ይኖርበታል'' ብለዋል። ከአማራ መገናኛ ብዙሃን የመጡት አቶ ደረጃ በበኩላቸው መንግስት ውስብስብ ችግሮችን መፈተሽና መፍታት እንደሚኖርበት ተናግረው፤ ''ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ዕርዳታ ማቅረብ ላይ ከማተኮር ይልቅ ቀድሞ መከላከሉ ላይ ማተኮር ይገባል'' ሲሉ ገልጸዋል። የመገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው ተከታታይ ዘገባዎችን በመስራት የችግሮቹን መነሻና መፍትሄ ቢያመላክቱ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ጠቁመው ጋዜጠኝነትን ለፕሮፓጋንዳ ከማዋል ይልቅ ግጭቶችን ለመፍታትና መፍትሄ ለመስጠት መጠቀም ተገቢ እንደሆነ አመላክተዋል። የሰላም ጋዜጠኝነትን በተመለከተ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንዳሉት፣ የመገናኛ ብዙሃን ባሙያዎች በሙያ ስነ ምግባር መመራትና በእውነት ላይ ብቻ በማተኮር መዘገብ አለባቸው። በጎ ነገሮችን በማጉላት፣ ከአድልኦ በመጽዳት፣ ሀቀኛ እና ገለልተኛ በመሆን በሙያ ስነምግባር በመመራት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት፤ ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማመላከት ላይ በመስራት አገራዊ ጉዳዮችን ማጉላት አለባቸው። ሚኒስቴሩ አሁን ላይ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን መፍታት ላይ ማተኮሩንና በዘላቂነት በአገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ  የ10 ዓመት የዘላቂ ሰላም ግንባታ ፍኖተ ካርታ እቅድ እያዘጋጀ መሆኑንም አስታውቀዋል። ሰላም ማስፈንን በተመለከተ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የንቅናቄ ስራ በቀጣይ የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመው ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በቋሚነት የምክክር መድረክ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም