በሑመራ በኩል ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች ከ24 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

69
ሑመራ ህዳር 15/2011 በሑመራ በኩል ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች ውስጥ ከ24 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገባቱን አስታወቀ። ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር ከስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ አለው። የሑመራ ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ አስተባባሪ ኮማንደር መሰለ ይማም ዛሬ ለኢዜአ  እንዳሉት በጣቢያው ባለፉት ሦስት ወራት የተገኘው ወደ ውጭ ከተላኩት የግብርና ምርቶች ሽያጭ ነው። ከምርቶቹ ሰሊጥ 150 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ 22 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ዋነኛው ምርት መሆኑንም አስረድተዋል። ቀሪው ገቢ ከእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ፣ ከቅመማ ቅመምና ከጥራጥሬ መገኘቱንም አስተባባሪው ተናግረዋል። ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በስድስት ነጥብ 2 ሚሊዮን ብልጫ ተመዝግቦበታል። ገቢው ብልጫ ያሳየው ሰሊጥ በመላክ ብቻ ተወስነው የቆዩት ላኪዎች ዘንድሮ ተጨማሪ ምርቶችን በመላካቸው ነው። የጣቢያው ሠራተኞች ያለ ዕረፍት በመሥራትና ለደንበኞች የሰጡት አገልግሎት ለገቢው ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የበላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ ተወካይ አቶ ታዘበ አስማማው ሰሊጥ ወደ ለቻይናና እሥራኤል ገበያ የሚያቀርቡ ቢሆንም፤ ዋጋው ከአገር ስለሚለያይ እየተጎዳን ነው ብለዋል። በአገር ውስጥ አንድ ኩንታል ሰሊጥ ከ4ሺህ 900 እስከ አምስት ሺህ ብር ተገዝቶ በ145 ዶላር ለውጭ ገበያ መቅረቡ አትራፊ እንዳላደርጋቸው  ገልጸዋል። ባለፉት ሦስት ወራት 3 ሺህ 800 ኩንታል ምርቱን ማቅረባቸውን በመግለጽ። ሰሊጥ በአገር ውስጥ ስለተወደደ ከምንልክባቸው አገሮች ዋጋ ጋር ሲነጻጸር በዋጋው ልዩነት ተጎድተናል የሚሉት ደግሞ የዋርካ ትሬዲንግ አስመጪና ላኪ  ድርጅት ተወካይ አቶ እምሩ ገብረ ሕይወት ናቸው። በሩብ ዓመቱ ከሰባት ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ወደ ቻይና፣ እሥራኤልና ሕንድ መላኩን ተናግረዋል። በሑመራ ጉምሩክ  መቅረጫ ጣቢያ በኩል ባለፈው ለውጭ ገበያ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ127 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም