ደደቢት በፕሪሚየር ሊጉ ለሶስተኛ ጊዜ ተሸነፈ

70
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ ደደቢትን 1 ለ 0 በማሸነፍ በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ አግኝቷል። በሃዋሳ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በበረከት ይስሃቅ ብቸኛ ጎል ፕሪሚየር ሊጉን ዘንድሮ የተቀላቀለው ደቡብ ፖሊስ አሸናፊ ሆኗል። በዘላለም ሽፈራው (ሞሪኒሆ) የሚሰለጥነው ደቡብ ፖሊስ በመጀመሪያ ጨዋታው በመከላከያ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት መሸነፉ የሚታወስ ሲሆን የዛሬው ድሉ ወደ አሸናፊነት መንፈስ እንደሚመጣ አድርጎታል። በአንጻሩ ደደቢት የዛሬውን ጨምሮ ሶስት የሊጉ ጨዋታችን የተሸነፈ ሲሆን በሊጉ ጥሩ ያልሆነ አጀማመር አሳይቷል። በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች በመቐለ ሰባ እንደርታና በኢትዮጵያ ቡና መሸነፉ ይታወቃል። የዛሬውን ሽንፈት ተከትሎ ክለቡ በአምስት የግብ እዳና ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃን ላይ ይዟል። የሶስተኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል በሽሬ ስታዲየም ስሑል ሽረ ከአዳማ ከተማ፣ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይጫወታሉ። ትናንት በሃዋሳ ስታዲየም በተደረገ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሲዳማ ቡናና ባህርዳር ከተማ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በአህጉራዊ የክለቦች ጨዋታና በተለያዩ ምክንያቶች መከላከያ ከድሬዳዋ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባ ጅፋር፣ ኢትዮጵያ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና መቐለ ሰባ እንደርታ ከፋሲል ከተማ ሊያደርጓቸው የነበሩ የሶስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ መራዘማቸው ይታወቃል። እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች መቐለ ሰብአ እንደርታና ኢትዮጵያ ቡና ስድስት ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ሲዳማ ቡናና ባህርዳር ከተማ በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አዳማ ከተማ፣ ደደቢትና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም