አልሸባብ በሶማሌ ክልል ችግር ይፈጥራል የሚል ስጋት የለም

104
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አልሸባብ ከጸጥታ ሃይሉ አቅም በላይ ሆኖ በሶማሌ ክልል ችግር ሊፈጥር እንደማይችል የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። መከላከያ ሰራዊቱ በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን ከህዝቡና ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን እያረጋጋ መሆኑን ገልጿል። የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ሜጄር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አልሸባብ ቀደም ሲል በተለይ በምስራቁ የአገሪቷ ክፍል በጸጥታና በልማት እንቅስቃሴው ላይ ስጋት ሲፈጥር መቆየቱን አስታውሰዋል። መከላከያ ሰራዊት ከፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች፣ ከክልል የጸጥታ ሃይሎችና ከህዝቡ እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች ጋር በመተባበር የአልሸባብን ጥቃት መመከት የሚችልበት ደረጃ ላይ መሆኑንም ነው ያመለከቱት። ''እንደ ወታደር አልሸባብ ጥቃት ከማድረሱ በፊት ክትትልና ስምሪት መደረግ አለበት'' ያሉት ሜጄር ጄኔራሉ ሶማሌ ክልል አሁን ካለው ያለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጥርለት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ የሀሰት ወሬዎችን በማቀናበር የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይኖር የሚያደርጉ አካላትን የህግ ተጠያቂ ለማድረግ መከላከያ ሰራዊት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት። በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አዋሳኝ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት መከላከያ ሰራዊቱን ጨምሮ ከብሄራዊ ደህንነትና መረጃ፣ ከክልል አመራሮችና ከፌዴራል ፖሊስ የተወጣጣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንና በአጭር ጊዜ ወደ እያንዳንዱ ቀበሌ በመግባት የማረጋጋቱን ስራ እንሰራለን ብለዋል። የጸጥታ ሃይሉ ዋና ስራ ሰላም በሌለባቸው አካባቢዎች ሰላም ማስከበርና ማረጋጋት በመሆኑ ህዝቡ ለሚያነሳቸው ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የፖለቲካ አመራሮች ፈጣን ምላሽ ካልሰጡ ችግሩ መልሶ ሊያገረሽ ይችላል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም