የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ከ2 ወር በኋላ መደበኛ ስርጭቱን ይጀምራል

73
ወልድያ ህዳር 15/2011 የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ከሁለት ወር በኋላ መደበኛ ስርጭቱን እንደሚጀምር ፕሬዚዳንቱ ገለጹ። የጣቢያው ሥራአስኪያጅ አቶ ኪዳነ ማርያም ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው የአካባቢውን ሕዝብ የመረጃ ተደራሽነት ለማስፋፋት ያቋቋመው ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ በጥር ወር መደበኛ ስርጭቱን ይጀምራል። ጣቢያው በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርናና ሌሎች ዘርፎች ያተኮሩ ፕሮግራሞች ይኖሩታል ብለዋል። እንዲሁም ወቅታዊ መረጃና የመዝናኛ ፕሮግራሞች እንደሚኖሩትም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። የሙከራ ስርጭቱን በአምስት ባለሙያዎች እየተመራ ካለፈው ወር ጀምሮ በሙከራ ስርጭት እያስተናገደ ያለውን ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ሥራ ለማስጀመር የ25 ባለሙያዎች ቅጥር እንደሚከናወን አስታውቀዋል። የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኛነትና ኮሙኒኬሽን የትምህርት ክፍል ተጠሪ አቶ ብርሃኑ ደጀኔ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ሬዲዮ ጣቢያውን መክፈቱ ለአካባቢው ኅብረተሰብ  መረጃ ለማድረስና ከማስተማር ባለፈ ወቅቱን ያገናዘበ ተግባር መሆኑን ይናገራሉ። ጣቢያው የትምህርት ክፍሉ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበላቸውን 100 ተማሪዎቹን በተግባር የተፈተነ ሙያ ይዘው ለመውጣት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማሀበረሰብ ተቀራርቦ ለመሥራት እገዛ ያደርጋል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስርጭቱን የሚያደርገው በኤፍ ኤም 89 ነጥብ 2 ነው።                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም