በባሌ ዞን የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎችና እገዛ ላደረጉ መምህራን ሽልማት ተበረከተ

70
ጎባ ህዳር 15/2011 በባሌ ዞን በሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች፣ እገዛ ላደረጉ መምህራንና ባለድርሻ አካላት የእውቅናና የገንዘብ ሽልማት ተበረከተ፡፡ ሽልማቱ ለላቀ ስራ እንደሚያነሳሳቸው ተሸላሚ ተማሪዎችና መምህራን ተናግረዋል፡፡ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ግዛው በሽልማት አሰጣጡ ስነስርዓት ወቅት እንደተናገሩት ሽልማቱ የተሰጠው በዞኑ በ2010 የትምህርት ዘመን ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ 22 ተማሪዎችና ሞዴል መምህራን ነው፡፡ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የአንድ ሺህ ብርና መጽሃፍት፣ በስራቸው ሞዴል ሆነው ለተመረጡ አራት መምህራን ደግሞ የአንድ ሺህ ብርና የምስክር ወረቀት መበርከቱን አመልክተዋል፡፡ በትምህርት አሰጣጥ ምርጥ ተሞኩሮን በማስፋትና የትምህርት ጥራት ፓኬጅን ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው አራት ትምህርት ቤቶችና ሶስት ወረዳዎች ዋንጫና  የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ በዞኑ ባለፈው ዓመት በተሰጠው የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና 98 ነጥብ 2 በመቶ፣ የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት መካከል 49 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም የ12ኛ ከፈል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱት መካከል 72 ነጥብ 5 በመቶ ወደ ቀጣዩ የትምህርት እርከን አልፈዋል፡፡ በሽልማት አሰጣጡ ስነስርዓት ወቅት የተገኙት በዞኑ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት የከተማ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ኤጄሬ "መንግስት በቀጣይነት በትምህርት ዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ህብረተሰቡን በሳተፈ መልኩ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራል" ብለዋል፡፡ በዞኑ የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለነበራቸው መምህራንና ባለድርሻ አካላትንም አመስግነዋል፡፡ ከተሸላሚዎች መካከል በጎባ ሁለተኛ ደረጃ በአስረኛ ክፍል አራት ነጥብ በማስመዝገብ የአንድ ሺህ ብር ተሸላሚ የሆነው ተማሪ አኒስ አብደላ በሰጠው አስተያየት "ሽልማቱ ጠንክሬ ለመማርና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መነሳሳትን ይፈጥርልኛል" ብሏል፡፡ "የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋን የማፍራት የመምህራን መደበኛ ስራ ቢሆንም ስራን ማዕከል ያደረገ የማትግያ ሽልማት ለላቀ ውጤት የሚያነሳሳ በመሆኑ ተደስቻለሁ" ያሉት ደግሞ ከጎባ ሁለተኛ ደረጃ በሞዴልነት የተሸለሙ መምህር ተሾመ አሰፋ ናቸው፡፡ በባሌ ዞን በ2011 የትምህርት ዘመን ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደረጃ ያላቸው ከ444 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች  ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ከዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም