በምስራቅ ወለጋ ዞን 19 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል

49
ነቀምቴ ግንቦት16/2010 በምሥራቅ ወለጋ ዞን እስካሁን 19 ሺህ ሔክታር የሚጠጋ መሬት በበቆሎና ማሽላ  ዘር መሸፈኑን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ገለፀ ። የጽህፈት ቤቱ የእርሻ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሽብሩ ጉርሜሣ እንደገለፁት በዞኑ በዘንድሮው የመኸር ወቅት 415 ሺህ 614 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ የእርሻና የዘር ስራ እየተካሄደ ነው፡፡ እስካሁን ታርሶና ለስልሶ ለዘር ከተዘጋጀው 313 ሺህ 164 ሄክታር መሬት ውስጥ በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም 18 ሺህ 995 ሔክታሩ በዘር ተሸፍኗል፡፡ በመኸር እርሻ ከሚለማው መሬት ውስጥ  169 ሺህ 656 ሄክታር የሚሆነውን በሙሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ በመሸፈን ምርታማነትን ለማሳደግ መታቀዱን አመልክተዋል፡፡ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግም የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ስርጭት እየተካሄደ  ነው፡፡ እስካሁንም 349 ሺህ 988 ኩንታል ማዳበሪያና ከ29 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ቀርቦ እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከልማቱ ተሳታፊዎች መካከል  የዲጋ ወረዳ የለሊሣ ዲምቱ ቀበሌ አርሶ አደር ግርማ ኢታና በሰጡት አስተያየት ያላቸውን 3 ሄክታር መሬት አርሰውና አለስልሰው ለዘር  አዘጋጅተዋል። የዝናብ ስርጭቱ በመልካም ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ ያዘጋጁትን ሶስት ኩንታል ማዳበሪያና ስድስት ከረጢት’’ሾኔ’’የተባለ ምርጥ የበቆሎ ዘር  በመጠቀም በቅርቡ እንደሚዘሩ አስታውቀዋል። ደጋግመው በማረስና በማለስለስ ካዘጋጁት አምስት ሄክታር መሬት ውስጥ   ግማሹን  በቆሎ መዝራታቸውን የገለፁት ደግሞ የዋዩ ቱቃ ወረዳ የቦነያ ሞሎ ቀበሌ አርሶ አደር በዳሣ ኦፍጋአ ናቸው፡፡ ቀሪውን ማሳ ደግሞ በአንድ ሳምንት ውስጥ በዘር ለመሸፈን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዘንድሮው የመኸር ልማት  ከ14 ነጥብ 4 ሚሊዮን  ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን እቅዱ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ምርት በ300 ሺህ ኩንታል ብልጫ አለው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም