የቡና ምርትን በብዛትና በጥራት ለማቅረብ ማነቆዎቹ እንዲፈቱ ተጠየቀ

198
መቱ ግንቦት 16/2010 የቡና ምርትን በብዛትና በጥራት ለገበያ ለማቅረብ በግብይት ሂደቱ እያጋጠሟቸው ያሉ ማነቆዎች እንዲፈቱላቸው በኢሉአባቦር ዞን በቡና ንግድ የተሰማሩ ባለሀብቶች ጠየቁ፡፡ በቡና ምርት ጥራት አጠባበቅ ዙሪያ የዞኑ አስተዳደር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡ በዚሁ ጊዜ ባለሀብቶቹ እንዳሉት  በምርት ገበያ በኩል በሚያደርጉት ግብይት ረጅም ሰአት ወረፋ በመጠበቅ ለመኪና ኪራይ ወጪ እንደሚዳረጉና በግብይቱም የሸጡበት የምርት መያዣ ጆኒያ ያለመመለስ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል ። ይህም  ምርቱን በሚፈለገው መጠንና ጥራት ለገበያ እንዳያቀርቡ ማነቆ እንደሆነባቸው ገልፀዋል፡፡ በመቱ ከተማ በግብይቱ የተሰማሩ አቶ ሀሰን ሲራጅ እንዳሉት ምርቱን በደሌ ድረስ ወስደው በምርት ገበያ በኩል  በሚሸጡበት ጊዜ ረጅም ወረፋ ስለሚጠብቁ በአንድ ጊዜ ለመኪና ኪራይ እስከ 25 ሺህ ብር ይከፍላሉ፡፡ ያለአግባብ የወጣውን ወጪ ለማካካስ  ከአርሶአደሩ ዋጋ ቀንሰው ለመግዛት እንደሚገደዱም ተናግረዋል፡፡ “ህገ ወጥ የቡና ንግድ እየቀነሰ ቢመጣም ሙሉ በሙሉ አልተወገደም'’ ያሉት ነጋዴው መንግስት “ችግሩን በመፍታት ረገድ  ከሚመለከተው አካላት ጋር በመሆን አፋጣኝ መፍትሄ ሊፈልግ ይገባል'' ብለዋል፡፡ በአልጌሳቺ ወረዳ በግብይቱ የተሰማሩ አቶ መለሰ አረጋ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መቱ ከተማ ላይ እንዲቋቋም በተለያዩ  ጊዜያት ቢጠይቁም እስካሁን  ባለመቋቋሙ ለከፍተኛ የመኪና ኪራይና  የተለያዩ እንግልቶች እየዳረጋቸው ነው፡፡ “የምርት ገበያ ይምጣ ብለን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን እኛ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና የዞኑ አስተዳደር ቦታ በማዘጋጀትና በሌሎችም የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል'' ብለዋል፡፡ በግብይት ሂደቱ በኩል እየታዩ ያሉትን ፈተናዎች በመቋቋም  ለምርቱ ጥራት መጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡ የኢሉአባቦር ዞን ቡና ሻይና ቅመማቅመም ልማት ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ከተማ አዲሱ እንዳሉት “ከዞኑ ለገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርትና ጥራት ለማሳደግ በመስኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት  ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው'' ብለዋል፡፡ በዞኑ ባለፉት 9 ወራት ከ25 ሺህ 300 ቶን በላይ ቡና ለገበያ መቅረቡን ገልፀው  የቀረበው ምርት ከእቅዱ በላይ ቢሆንም በጥራት በኩል ክፍተት መኖሩን  ተናግረዋል፡፡ የምርት መያዣ ጆንያ እንዲመለስ የሚያስገድድ  መመሪያ በመኖሩ  በአግባቡ ካልተመለሰ በህግ አግባብ መጠየቅ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ ቡና ከመሰብሰብ ባሻገር ለጥራቱ መጠበቅ ከአምራች አርሶአደሩ ጋር በቅርበት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መቱ ከተማ ላይ ቅርንጫፍ በመክፈት  በቅርበት አገልግሎት እንዲሰጥ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ቦታ መዘጋጀቱን አስረድተዋል ፡፡ የኮንትሮባንድ ንግዱ ቢቀንስም የዞኑ ቡና  በህገወጥ መንገድ ሲወጣ  በጅማ፣ ነቀምትና ደምቢዶሎ አካባቢዎች መያዙን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው ህገወጥ ንግዱን ለመከላከል የተጠናከረ ቁጥጥር በማድረግ  አጥፊዎቹን  ወደ ህግ ለማቅረብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተወጣጡ በቡና ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በምርቱ ጥራት አጠባበቅ  በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡ በኢሉአባቦር ዞን 13 ወረዳዎች ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ምርት እየለማ ሲሆን  ከ150 ሺህ በላይ አርሶአደሮች የልማቱ ተሳታፊ መሆናቸውን ከዞኑ ቡና ፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም