የፖሊስ አባላት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል- ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ

1826

አዳማ ህዳር 15/2011 የፖሊስ ሠራዊት አባላት ሙያዊና ህገ- መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰቡ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በፖሊስ ሳይንስና ወንጀል መከላከል  ለአንድ ዓመት ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች ዛሬ አስመርቋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አለማየሁ እጅጉ በምረቃ ስነ- ስርዓት ወቅት እንደተናገሩት ላይ የፖሊስ ሠራዊት አባላት በክልሉ የህግ የበላይነት መረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

“የክልሉን ሰላም ለማወክና የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎች አሁንም እንቅስቃሴያቸውን ቀጥለውበታል” ብለዋል።

በተደራጀ ሌብነትና ዝርፊያ ውስጥ የገቡና ለውጡ ጥቅማቸውን የነካባቸው ኃይሎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ጭምር በመግባት አፍራሽ ተልዕኳቸውን  ለመወጣት እየሚከሩ መሆናቸውን  ጠቅሰዋል።

አፍራሽ ተግባራቸውን ማምከንና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ  የፖሊስ ሠራዊት አባላት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

የፖሊስ ሠራዊት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለውጡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ያሳዩትን ቁርጠኝነት የሚበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።

“በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ  አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ሂደት ውስጥ የፀጥታ አካላት ግንባር ቀደም ሚናቸውን በመወጣት ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል” ሲሉም አሳስበዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ተፈራ ዳባ በበኩላቸው ኮሌጁ የክልሉን ፖለስ ሠራዊት አቅም የማብቃትና ሳይንሳዊ እውቀት የማስጨበጥ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል ።

“የፀጥታ አካላትን በአመለካከት፣ አስተሳሳብና በእውቀት ማብቃትና ከለውጡ ጋር መራመድ እንዲችሉ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ኮሌጁ ዛሬ ያስመረቃቸው 300 ከፍተኛ መኮንኖች በወታደራዊፖሊሳዊ ሳይንስ፣ በህገ- መንግስታዊ መርሆዎች፣ በሥነ ምግባር፣ በወንጀል መከላከል፣ በፆታ እኩልነት፣ በሴቶችና ህፃናት ጥቃት መከላከል ለአንድ ዓመት የተሰጣቸውን ስልጠና በአግባቡ ያጠናቀቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“በህግ- ማስከበር ሂደት ውስጥ የፖሊስ ሠራዊት ሚና ከፍተኛ ነው” ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ፤ መኮንኖቹ በኮሌጅ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ረዳት ኢንስፔክተር ሀሰን አማን በሰጡት አስተያየት በስልጠናው ፖሊሳዊ ሳይንስን በአግባቡና በጥልቀት መገንዘባቸው ገልጸዋል።

በክልሉ ሥርዓት አልበኝነትን በማስወገድ የህግ የበላይነትን ለማረጋጋጥ የሚያስችል ተጨማሪ አቅም መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሰንቀሌ ኢንስቲትዩት ማሰልጠኛ ለ27ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸው 6ሺህ የፖሊስ አባላት በቅርቡ አስመርቋል፡፡