በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የሜቴክ አመራሮች መከላከያን አይወክሉም ተባለ

92
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ የስራ አመራሮች በመከላከያ ሰራዊት ስር አለመሆናቸውን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። ከሜቴክ አመራሮች ክስ ጋር ተያይዞ አጠቃላይ የመከላከያ ሰራዊቱን ስም የማጥፋት ዘመቻ የሚያካሄዱትን የህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግም አስጠንቅቋል። የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የተያዙ የሜቴክ የቀድሞ አመራሮች የአገር መከላከያ ሰራዊትን የሚወክሉ አይደሉም። በተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ምክንያት አጠቃላይ ሰራዊቱ የሙስና ችግር እንዳለበት ተደርጎ እየተካሄደ ያለው ስም የማጥፋት ዘመቻ የመከላከያ ሰራዊቱን እስከ ሞት የደረሰ የህይወት መስዋዕትነት ዋጋ የሚያሳጣ ነው ብለዋል። የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ቀደም ሲል በመከላከያ ሚኒስቴር ስር ካሉ የልማት ድርጅቶች አንዱ የነበረ ሲሆን በሌሎችም ተቋማት ያሉ የልማት ድርጅቶች በኮርፖሬሽን ደረጃ በአዋጅ እንዲቋቋሙና በቦርድ እንዲመሩ ተጠሪነታቸውም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንዲሆን ተደርጓል። እንደ ሜጄር ጄኔራሉ ገለጻ ሜቴክ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን፣ ሲቪል ተቀጣሪዎችና የተለያዩ አማካሪዎችን በመያዝ ራሱን ችሎ በአዋጅ የተቋቋመና በቦርድ የሚመራ ተቋም ሆኖ ዓመታትን አስቆጥሯል። እዚያ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶቹ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ሲቪል የተቀየሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ የደንብ ልብሱን ለብሰው መንግስት በሚያወጣቸው መስፈርቶች መሰረት የማዕረግ ዕድገት እየተሰጣቸው የቀጠሉ አመራሮች እንደነበሩ ሜጄር ጄኔራል መሐመድ ገልጸዋል። በመሆኑም ራሱን ችሎ በቦርድ በሚመራ ተቋም ውስጥ ያሉ ጥቂት ግለሰቦች የፈጸሙትን የወንጀል ድርጊት መላው መከላከያ ሰራዊት እንደፈጸመው አድርጎ ስም ማጥፋት ተገቢ አይደለም ብለዋል። ሰራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ተሳትፎ ራሱን ነጻ አድርጎ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የህዝቦች ጥቅም የሚያረጋግጡ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን እየተወጣ ነው ሲሉም ተናግረዋል። የአገር መከላከያ ሰራዊት በመንግስት የተጀመሩ ጥፋተኞችን ለይቶ የመያዝ እርምጃዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩሉን ድጋፍ ያድርጋልም ብለዋል። በአገሪቱ እዚህም እዚያም የሚነሱ የጸጥታ ስጋቶችን ቀድሞ በማወቅና በመመከት የተጀመረውን አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚደግፉም ነው የገለጹት። የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በደንብ ቁጥር 183/2002 ዓም የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው። ሜቴክ ከ2004 እስከ 2010 ዓ.ም ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ አገር ግዥ ያለጨረታ ከመፈጸሙ ጋር ተያይዞ የተቋሙ የስራ ኃላፊዎችና በወንጀሉ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም