እንደአገር ያለብንን የሐሳብ ድርቀት መፍታት ዋነኛው ትኩረታችን መሆን አለበት ፡-አቶ ልደቱ አያሌው

277
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው አቶ ልደቱ አያሌው እንደአገር ያለውን የሐሳብ ድርቀት መፍታት ዋነኛ ትኩረት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ልሂቃን 'የፖለቲካ ማሻሻያ' በሚል እየተወያዩ ይገኛል። በመድረኩ አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ ሐሌሉያ ሉሌና አቶ ሌንጮ ለታ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ አቅርበዋል። አቶ ልደቱ በመነሻ ጽሁፋቸው ላይ እንደገለጹት፤ እስካሁን በነበረው የፖለቲካ ጉዞ የፖለቲካ ፍልስፍናዎችን ከውጭ ኮርጆ የማምጣት ልምድ እንጂ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማጣጣም ልምድ የለም። እንደ ዴሞክራሲ፣ ፌዴራሊዝምና ሌሎች የፖለቲካ ፍልስፍናዎች  የሚያግባቡ ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እንዴት መተግበር እንደሚገባቸው በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። የፖለቲካ ፍስፍናዎቹን ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማጣጣም ስራ አለመሰራቱን የተናገሩት አቶ ልደቱ የፖለቲካ ልሂቃኑ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግር የሚችል የፖለቲካ ሐሳብ ይዘው ሊመጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የፖለቲካ ጉዞው ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ለመውሰድ የሚያስችል ፖለቲካዊ አስተዳደርና አመራር በሐሳብ ድርቀት የተመታ እንደነበር ተናግረዋል። ''የሐሳብ ድርቀቱን ለመፍታት የፖለቲካ ልሂቃኑ ብቁ ሆነው መገኘት አለባቸው'' ብለዋል አቶ ልደቱ። በሌላ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ሐሌሉያ ሉሌ በበኩላቸው ብዙሃኑን ያማከለና ያሳተፈ ስርዓት መፍጠር ካልተቻለ ትርጉም ያለው ዴሞክራሲ መፍጠር አዳጋች እንደሚሆን ጠቁመዋል። እስካሁን በነበረው የፖለቲካ ሂደት ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ገለልተኛ አካላት ህዝቡን ያሳተፉ እንዳልነበሩ ገልጸዋል። በፖለቲካ ሜዳው ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ውስን መሆንና ብዙሃኑ በቂ ተሳትፎ የማያደርግ መሆኑ ሂደቱን እንደጎዳው ተናግረዋል። ይህንን ለመቀየርና ብዙሃኑን ያሳተፈ ምህዳር ለመፍጠር ጠንካራ፣ ባለብዙ አማራጭ አቅምና አቋም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ሶሳይቲ አስፈላጊ መሆናቸውን አቶ ሐሌሉያ አስረድተዋል። አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው አገሪቱ እስካሁን የነበራትን የፖለቲካ ታሪክ ሙሉ ለሙሉ የቀየረ ለውጥ ማካሄድ እንደተቻለ ተናግረዋል። ''በመሆኑም ደም መፋሰስና የተገነባውን የማፍረስ ባህል ቀርቶ በውይይትና በንግግር አገር የምንቀይርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል'' ብለዋል። እንደአገር አንድ የሚያደርጉ ሐሳቦችን ማዳበር፣ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣትና መፍታት እንዲሁም የተለያየ አመለካከትን አቻችሎ መሄድ አንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የመጣውን ለውጥ በድርጅት ደረጃ የሚቃወም ባይኖርም በግለሰቦች ደረጃ የሚቃወሙ አካላት መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሌንጮ ተቃውሞውን ለመፍታት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም