የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሕዝብን የማገልገል ዓላማ ዘንግተው የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ ሆነው ቆይተዋል-ምሁራን

53
ባህር ዳር ህዳር 15/2011 የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተቋቋሙለትን የልማት ጋዜጠኝነትን በማራመድ ሕዝብን የማገልገል ዓላማ ዘንግተው የፕሮፖጋንዳ ማስተላለፊያ ሆነው መቆየታቸውን አንድ ምሁራን አመለከቱ። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ትምህርት ክፍል ''የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ከለውጡ በፊት የነበሩበትና ከለውጡ በኋላ ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል? '' በሚል ዐውደ ጥናት አካሂዷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ ጥናት አማካሪ ዶክተር ሙላቱ ዓለማየሁ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አገሪቱ በምትከተለው ሥርዓት ሕዝብን የማገልገል መርህ ሲሰበክ የቆየ ቢሆንም መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት አፈቀላጤ ብቻ ሆነው አሳልፈውታል። የልማት ጋዜጠኝነት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለመንግሥት የሚጠቅሙ አቅጣጫዎችን ለመጠቆምና ለማስገንዘብ እንደሚችል ቢታመንበትም፤መገናኛ ብዙኃን  ከመንግሥት የሚነገራቸውን ስኬቶችን ብቻ ሲተርኩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። መገናኛ ብዙኃን ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ለመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥና ሲመረቁ ብቻ ሲዘግቡ ነበር ያሉት ምሁር፣ በሂደቱ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችንም እንዳይዘገቡ ፖለቲካ ሥርዓቱ ተጽዕኖ ያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል። ''ትክክለኛውን  የልማታዊ ጋዜጠኝነት  መመሪያ ሲተገብሩ የነበሩ የግል መገናኛ ብዙኃን እንዲዘጉ ተደርጓል፣ጋዜጠኞችም በአሸባሪነት እየተፈረጁ እንዲታሰሩና ከአገር እንዲወጡ ተደርገዋል” ብለዋል። በዚህም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እድገት እንዲቀጨጭና ሕዝብ አመኔታ ሲያጣባቸው መቆየቱን ምሁሩ አስረድተዋል። ከለውጡ በኋላ ለውጥ እያታየ መምጣቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ፣የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና ፋና ራዲዮና ቴሌቪዥን ሕዝብን ያማከሉ ዘገባዎች ለመሥራት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን በአብነት ጠቅሰዋል። ከለውጡ በኋላ በተወሰዱ እርምጃዎች  የመንግሥትም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙኃን አንጻራዊ ነጻነት ያሳዩ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሙላቱ ፣ መንግሥት ነጻነትን መፍቀድ ከቻለ የሕዝብን ብሶት ማሰማትና መንግሥትን አቅጣጫዎችን መጠቆም የብዙኃን መገናኛ ድርሻ ይሆናል ብለዋል። “የመንግሥትም ሆኑ የግል መገናኛ ብኃን ከለውጡ በፊት በነበረው ሁኔታ ምን ልስራ ብለው ሳይሆን፤ ይህን ስሩ ተብለው ተገደው ሲሰሩ ቆይተዋል”ያሉት ደግሞ ሌላኛው ጥናት አቅራቢ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት መምህር ዶክተር ጀማል መሐመድ ናቸው። መገናኛ ብዙኃን ችግሮችን ነቅሶ መፍትሄ እንዲገኝላቸው መናገር ሲገባቸው በነበረው በፖለቲካ ጫና መንግሥት የሚፈልገውን መረጃ ብቻ ሲያስተላልፉ በመቆየታቸው ሕዝብ ሲጠላቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ለውጡ በፈጠረው ምቹ አጋጣሚ በአገር ውስጥ የነበሩት ብቻ ሳይሆኑ፤ በአሸባሪነት የተፈረጁ መገናኛ ብዙኃን ጭምር አገር ውስጥ ገብተው መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ዶክተር ጀማል አመልክተዋል። ሕዝቡም የመረጃ አማራጮችን የመከታተልና የሚፈልገውን መረጃ የማግኘት ዕድሉ መስፋቱን ተናግረዋል። ነገር ግን አንዳንድ የክልል መገናኛ ብዙኃን ዘላቂ ሰላምና ልማትን ከመዘገብ ወጥተው ጽንፍ የወጣ ሕዝቦችን የሚያጣላ ዘገባዎችን በማስተላለፍ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።ይህም የአገሪቱን አንድነትና የሕዝቦችን ትስስር የሚያጠናክር ሳይሆን፣ መቃቃርንና ጥርጣሬን ይዘራል ብለዋል። ስለሆነም መገናኛ ብዙኃን ሕዝብ ለዘመናት ተነፍገውት የነበረውን ነጻነት ለመልካም ነገር ማዋል እንጂ፤ ነጻነቱ ስለተገኘ መረን የወጣ ዘገባ ከመዘገብ መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል። መንግሥትም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የሚገዙበት የተደራጀና ወጥ የሆነ የሚዲያ ፖሊሲ መቅረጽና ከፖሊሲው ውጪ የሚራመዱ መገናኛ ብዙኃን የሚገስጽ ተቋም ማደራጀት ይጠበቅበታል። በዐውደ ጥናቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት መምህራን፣የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም