የሲዳማና ወላይታ ህዝቦችን ትስስርን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ

1715

ሶዶ ህዳር 15/2011 የሲዳማና ወላይታ ህዝቦች ትስስርና ሰላም ዘላቂ ሆኖ እንዲጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለጠብ የሚያነሳሳ ታሪካዊ ቁርሾ እንደሌላቸውና ለግል ጥቅማቸው ጥላቻን የሚዘሩ  ኃይሎችን ለማሳፈር የህዝብ ለህዝብ  ትስስርን እንደሚያጠናክሩ አስተያየት ሰጪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ የሃገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ቶምቦላ ቶርባ እንደገለጹት የሲዳማና የወላይታ ህዝብ በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ሳይለያይ ችግሮችንም በጋራ እየተጋፈጠ የመጣ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት የተከሰተው ግጭት በባህላዊ ሽምግልና የተፈታ ቢሆንም ዘላቂ መሰረት እንዲኖረዉ ለጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል፡፡

የህዝብን ሰላም በማናጋት ለግል ጥቅማቸው የሚሰሩ ኃይሎችን ማሳፈር እንደሚገባና መንግስትም የህግ የበላይነት እንዲከበር የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህርት አልማዝ አንጁሎ በበኩላቸው በእርቀ ሰላም ሂደት
ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ ገልጸው “ ሂደቱ ውጤታማ የሆነው ሁለቱም ህዝቦች ሰላም ፈላጊና አብረው የኖሩ በመሆናቸው ነው” ብለዋል፡፡

ጥላቻን እያቀጨጩ ለመሄድ ከግለሰብ ጀምሮ በማህበራዊ እሴቶች ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናገረዋል፡፡

ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደቀያቸው ለመመለስ ህዝብና መንግስት ያደረጉት ጥረት የሚያስመሰግንና ለእርቀ ሰላሙ ሂደት አቅም እንደፈጠረም ገልጸዋል፡፡

” መቀራረብና ሰላምን ማሰብ ትርፍ እንጂ ጉዳት የለውም”” ያሉት አስተያየት ሰጪዋ በኃይል መብት ለማስከበር ችግርን የሚያነሳሱ ግለሰቦች ሰላም የማይፈልጉና ለህዝብ የማያስቡ  እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

” የሰው ልጆች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እንኳን ቢሆን ሰላምን መጠበቅ ምን ያህል ተገቢ መሆኑን አይተናል” ያሉት ደግሞ የሲዳማ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ያምሮት ኃይሌ ናቸው፡፡

አለመግባባቶችና ግጭቶች ተፈጥሮአዊ ቢሆኑም አውዳሚና ታሪክ የሚያበላሽ ሂደትን መከተል የህዝብን ሰላም ለማይመኙ አካላት ስኬት ቢመስልም ተወቃሽ ከመሆን እንደማያድን ተናግረዋል፡፡

ተከስቶ የነበረው ችግር ሁለቱንም ህዝቦች እንደማይገልጽ ጠቅሰው የእርቀ ሰላም ሂደቱን እስከታች ድረስ በማስተማር በተለይ ህዝብ ለህዝብ ትስስሩ እንዲጠናከር  እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዋ እንዳመለከቱት  በማህበራዊ ሚዲያዎች የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ የሚሰሩ ሰዎች ሊጠነቀቁ ይገባል  ፡፡

” ሰላም ሲደፈርስ በተለይ ሴቶች፤እናቶችና ህጻናት ለከፍተኛ ችግርና ጭንቀት ተጋላጭ በመሆናቸው አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የመደማመጥና ከአባቶች ያየነውን ባህልና እሴት በማዳበር የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ አለብን ” ብለዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ በተላ ባረና እንዳሉት ህዝቡ በራሱ ፍላጎት የሰላምና ዕርቅ ኮንፈራንስ ማካሄዱ በተለይ ለንግዱ ማህበረሰብ መረጋጋትን የፈጠረ ነው፡፡

በህዝቡ መካከል ያደረ ቁርሾ ሳይኖር በጥቂት ግለሰቦች አነሳሽነት የተከሰተ ግጭት መሆኑን በመገንዘብ  የተፈጠረው  ሰላም ዘላቂ መሰረት እንዲኖረው የንግዱ ማህበረሰብ የአቻ ግንኙነት በማካሄድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ  እንደሃገር ተረካቢ በተረጋጋና በሰከነ የኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንዳለበት  አመልክተዋል፡፡

በሲዳማና ወላይታ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት ህዳር 9/2011ዓ.ም. በሃዋሳ ህዳር 11 9/2011ዓ.ም. ደግሞ በወላይታ ሶዶ  የይቅርታና የእርቀ ሰላም ኮንፍረንስ መካሄዱን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡