“ብሄርተኝነት የጋረደው…˝

2126

በዘመናት መካከል በአለም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከርዕዮት አለማቸው ጋር ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ከነዚህ መካከልም መልካም ፍሬ አፍርተው ከዳር የሚደርሱ እንዳሉ ሁሉ በሚያራምዱት የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ርዕዮት አለም ምክንያት ከአለም ጋር ተላትመው በፍጥነት የሚከስሙም ቀላል አይደሉም፡፡ እንደ ናዚ አይነት ፓርቲዎች ከአቃፊነት ይልቅ ነቃፊነትን አንግበው፣ ከኛ በላይ የሰው ዘር ለአሳር ብለው በግብዝነት ተነሱ፡፡ ለጊዜውም ቢሆን አውሮፓን አመሰ ብዙ እልቂትም አስከተለ፡፡ፓርቲው በሚያራምደው ጽንፈኝነት ሳቢያም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ተጨፈጨፉ፡፡ የግብዝ ብሄርተኝነት የወለደው ጦስ  ሰብአዊነትን  ክዶ እልቂትን አስከተለ፤  አለምም ይህን የጎመዘዘ ሀቅ  የታሪኳ አካል አድርጋ ከመመዝገብ ውጭ ሌላ ምርጫ አልነበራትም፡፡

የናዚ እህት ድርጅት የሆነው ፋሽዚም ደግሞ ያገኘውን ሁሉ ጥረግ የሚል እኩይ አላማ ይዞ ከዚሁ አህጉር ተነሳ። ባህር ተሻግሮ ወደ  አፍሪካ ምድርም ገሰገሰ፤ ይባስ ብሎ የኢትዮጵያን  ምድር ረገጠ፡፡ በኢትዮጵያውያን አርበኞች ድል ተመቶ እስኪባረር ድረስ ለአምስት አመታት ያህል ቀላል የማይባል ግፍና መከራ ፈጽሟል፡፡ አለፍ ሲልም ለቅኝ አገዛዙ እንዲያመቸው ኢትዮጵያን በብሄርና  በሀይማኖት ለመከፋፈል የጠነሰሰው ሴራ ዛሬም ድረስ ቁርሾ ሆኗል፡፡

ከዚህ የምንረዳው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያራምዱት ርዕዮተ አለም የተዛባና ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ  ከሆነ ምን ያህል ለእልቂትና ጥፋት ሊዳርግ እንደሚችል ነው፡፡

ወደ አፍሪካ አህጉር ስንመጣ ደግሞ ዛሬ ዛሬ ሁለም ሀገራት ለማለት በሚያስደፈር ሁኔታ  የመድበለ ፓርቲን ይፈቅዳሉ፡፡

በብዝሃነት የበለጸጉ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲዋቀሩ በምን አይነት መንገድ መሆን እንዳለበት ህግና ደንብ  ያወጣሉ፤  ምክንያቱ  ደግሞ  የዘር ፖለቲካ  ያስከተለባቸውን  መራራ ታሪክ  ከቶውንም  መድገም አልፈለጉምና፡፡ ከዘር ፖለቲካ ይልቅ አካታችነትን ያስቀድማሉ፡፡

የጎረቤት ሀገር ኬንያን ብናይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲመሰረቱ ብሄርን አልያም ሀይማኖትን መሰረት አድርገው መሆን እንደሌለበት በህግ ተደንግጓል፡፡

በሩዋንዳ የዘር ፖለቲካ የወለደው ጥላቻ እኤአ በ1994 በመቶ ቀናት ብቻ 800 ሺህ  ቱትሲዎችን በሁቱ አክራሪ ብሄርተኞች መገደላቸው በጥቁር መዝገብ ታሪክ ላይ ሰፍሯል፡፡  በብሄር  ፖለቲካ ጫፍ የረገጡ አካላት በለኮሱት እሳት የአንድ ሀገር ህዝቦች እርስ በእርሳቸው  ተጨራረሱ፡፡  በአፍሪካ አህጉርም እጅግ አሳዛኙ ታሪክ  ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከስህተታቸው የተማሩት ሩዋንዳውያንም ያለፈውን አስከፊ ታሪካቸውን እርግፍ አድርገው ትተው ይቅር ተባባሉ፤ ብሄራዊ አንድነታቸውንና ደህንነታቸውን በማጠናከርም ሀገራቸውን በመገንባት ላይ ተጠምደዋል፡፡ ስለ ብሄር ወይም የዘር ልዩነት እያነሱ መቆራቆስ አይፈልጉም፡፡ ምክንያቱም የዘር ፖለቲካ ምንያህል አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዳስከፈላቸው ከእነሱ በላይ የሚያውቀው የለምና፡፡

ፖለቲከኞቻቸውም ቢሆኑ ርካሽ  የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብለው ስላለፈው አሳዛኝ ታሪካቸው እያነሱ መነታረክ አይፈልጉም፡፡ በእንዲህ አይነት ተግባር የሚሰማራ ፖለቲከኛ ካለም እንደ አላዊቂ ተቆጥሮ ይወገዛል እንጂ አድናቆትና ድጋፍ አይጎርፍለትም፡፡ “ብልህ ከጓደኛው ይማራል” እንዲሉ የሀገራችን ፖለቲከኞችም የዚህ ዓይነት በጎ ተሞክሮዎችን መጋራት ቢችሉ  አሸናፊነትን ይቀዳጃሉ እንጂ የሚያጡት ነገር አይኖርም፡፡ አሁን አሁን የሚታየው ሁኔታ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሚያራምዱት የመደመር ፖለቲካዊ ስሌት በማፈንገጥ በዘር ፖለቲካ ጡዘት የዜግነት ፖለቲካ ኮስምኖ የብሄር ፖለቲካ ጣራ ነክቷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፈር እየለቀቀ የመጣው የብሄር ፖለቲካ በሀገሪቷ ላይ ቀላል የማይባል ስጋትን ደቅኗል፡፡ እንዴት ከተባለ? ከእኛነት ይልቅ እኔነት ጎልበቶ በህዝቦች መካከል መጠራጠር ማሳደሩ ከማንም የተሰወረ  አደለም፡፡

እኔነትና ለኔ ብቻ የወለደው  እሳቤ ዜጎች ለዘመናት  ከኖሩበት ቀያቸውና ካፈሩት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በሀገር በውስጥ መፈናቀል ከአለም ቀዳሚዋ ሀገር እንደሆነችም እየተነገረ ነው፡፡ ይሄን ምን አመጣው? ሲባል ኢትዮጵያውያን ክፉ ስለሆኑ፣ አብረው መኖር ስለማይፈልጉ አይደለም፤ ይልቁንም ወቅቱ የወለደው ኢላማውን የሳተ የፖለቲካ እሳቤ እንጂ፡፡ የችግሩን ክፋት በመረዳትም የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከተሉት ርዕዮት አለም፣ አክቲቪስቶች የሚያራምዱት አስተሳብ ከሀገሪቱ ብሎም ከአለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሊያመዛዝኑትና ሊያመሳክሩት ግድ ይላቸዋል፡፡

ለመማር ዝግጁ ለሆነ ሁሉ ዛሬ ላይ በርካታ እድሎች አሉ፤ እርቀን ሳንሄድ ኢትዮጵያ ያሳለፈቻቸው አዎንታዊና አሉታዊ ክስተቶች፣ በአንድ አንድ የአፍሪካ ሀገራት በዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ያስከተለው እልቂትን ጨምሮ በአለም ላይ የነበሩ ታሪካዊ  ክስተቶች ዛሬ የምናራምደው ፖለቲካ  የት እንደሚያደርሰን ጭምር  አጉልቶ የሚያሳየን መነጸር ነው፡፡

ማንም በራሱ ላይ እዲደርስ የማይፈልገውን መፈናቀል፣ በማንነት መጠቃትና መሰል ተግባራትን  መጸየፍ ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከየትኛውም ብሄር፣ ሃይማኖት ጋር በተጸራሪ ሊንቀሳቀሱ አይገባም፡፡ ይህ ካልሆነ ግን “ሩጫው ለማንም የማትሆን ሀገር ለማድረግ ነው” እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ውጤቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ ያው መጠፋፋት፡፡

መደመርን ማጠናክር፣ በሂደት ላይ ያለውን የለውጥ ጉዞ ከዳር ማድረስ፣ በሃሳብ ልቆ  መገኘት፣ አካታችነትን ማራመድ ለሁሉም የሚበጅ ተግባር ነው፡፡ ተበድለናል፣ ተገፍተናል የሚል የእሮሮ ፖለቲካ የት ያደርሳል? ይህ እስካል ተወገደ ድረስ ከዚህ አዙሪት መውጣት ይቻል ይሆን? ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር መምህር  ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ ሀገሪቱ የምትከተለው የፌዴራሊዝም ስርዓት ብሄር ተኮር መሆኑ ጥቅምና ጉዳት   አለው ይላሉ።

“ከሁሉ በላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ሲሾሙ መጀመሪያ መታየት ያለበት መስፈርት ብቃት ነው፡፡ ብቃት በስራም በትምህርት ሊደገፍ ይችላል፤ የስራ ውጤት በስራ ላይ በቆዩበት ወቅት ያስመዘገቡት የስራ ውጤት ምን ይመስላል የሚለው ታሳቢ መደረግ አለበት።” ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ።

ከፍተኛ አመራር ላይ የሚመደቡ አካላት ከህብረተሰቡ ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ ስነምግባር፣ ለሀገር ባላቸው አተያይ ከሆነ እንጂ ስራዎችን ከራሱ ብሄር ጋር የሚያይ አክራሪ ብሄርተኛ  በፌዴራል መዋቅር ላይ መግባት እንደሌለበትም ያነሳሉ።

አሁን ያለው የፖለቲካ ድርጅቶች ባህሪ ብሄር ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀት በመሆኑ ሁልጊዜ ወደራስ መመልከትን ያላብሳል፣ ስግብግብነትን ያመጣል፣ ስልጣን ለመያዝ ሲባል ብቻ ያለ የሌለውን ሁሉ እንደ ችግር እያነሱ የኔ ብሄር ተጎዳ ወይም የኔ ብሄር ተገለለ፣ ተገቢውን ቦታ አላገኘም የሚል ውዝግብ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን ነው  ምሁሩ በአሉታዊ የጠቀሱት።

በቅርቡ መንግስት ያዋቀረው ካቢኔ በአንጻራዊነት የተሻለ መሆኑን  የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ “ሚኒስትሮች የተመደቡበትን ተቋም አንደኛውን ከሌላው ከፍና ዝቅ አድርጎ የማየት ዝንባሌ ግን ተገቢ አይደለም፤ ሁሉም ሚኒስትሮች የሚወስኑት እኩል ነው፤ ሹመቱም በአንጻራዊነት ተመጣጣኝ ነው ብዬ አስባለሁ፤ ውክልና ከሌላቸው ክልሎች ውጭ” ነው ያሉት።

የተማሏ ነገር በአንድ ጊዜ መጠበቅ ይከብዳል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፤  ዶክተር አቢይ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወይም ክልሎች ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ የካቢኔ ውክልና እያገኙ  መሆኑና  በሚኒስትር ዲኤታዎች፣ በዳይሬክተሮች የሚመሩ ተቋማት  ላይም የማመጣጠን  ሥራ እየተሰራ  መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

“ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹ በውስጣቸው የሚፈጥሩት በቂ የድርጅት ውክልና አላገኘንም የሚሉ የጨዋታ ብልሽቶች አሉ፤ ይህ ብልሽት እስከ ህዝቡ ወርዶ ለስልጣን ያለ አተያይ ከራስ ወገን ብቻ እንዲሆን አድርጓል” ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ  ጉዲና ናቸው።

በየትኛውም ሀገር ቀውስ ሲያጋጥም የተለያየ አቋም ያላቸው የፖለቲካ ሃይሎች ምን እናድርግ ወደሚል መወያየት ይመጣሉ ያሉት ዶክተር መረራ በእኛ ሀገርም የፖለቲካ ሃይሎች ልዩነታቸውን ይዘው በሴራ ሲሸራረቡ እና በነገዋ ኢትዮጵያ ላይ ከመምከር ይልቅ መገፋፋት እና አንዱ በአንዱ ላይ ሲነሳ  የኖሩ በመሆኑ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያብራሩት።

ካቢኔውን ብቻ መተቸት ትክክል አይመስለኝም ያሉት የአረና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አቶ ገብሩ አስራት ስልጣን ሲሰጥ የአንዱ ብሔር የበዛ የአንዱ ያነሰ ሊሆን ይችላል፤ ዋናው  ከፍትህ፣ ከዴሞክራሲ፣ ከነጻነት፣ ከስራ አጥነት አንጻር ምን አዲስ ፖሊሲ ወይም ለውጥ ይዞ መጣ የሚለው ላይ ሊተኮር እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

ከስልጣን ሹም ሽርና ከውክልና ጥያቄ ባለፈ ሀገሪቱ በውስጥ ሰላም የከፋ ሁኔታ ላይ መሆኗ፣ ኢህአዴግ በራሱ ባመጣው የጽንፍ አስተሳሰብ ሁሉም ለየራሱ ቅድሚያ እንዲሰጥ ማድረጉን  የሚገልፁት አቶ ገብሩ ችግሩም ለውጥ ሲመጣ ይቀረፋል ብለዋል። ለችግሮቹ መፍትሔ ለመስጠትም መንግስት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ህዝቡና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት ውይይት በማድረግ ወደ ብሄራዊ መግባባት መምጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ችግሮች ሲከሰቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸውን ቁጭ ብሎ ልዩነቶችን አቻችሎ  በመነጋገር መፍታት እንጂ አካኪ ዘራፍ የሚለው አካሄድ  አይጠቅምም ያሉት አቶ ገብሩ በዚህ አካሄድ ሀገር በተለይ ወጣቱ እጅጉን ስለሚጎዳ መግባባት ላይ ለመድረስ መወያያት አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት።

ሀገራት የየራሳቸው ጎልቶ የሚወጣ የማንነት መገለጫ  እንዳላቸው  የሚገልጹት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ፤ በኛ ሀገር የብሄር ማንነት ለበርካታ አመታት  ጎሎቶ የወጣ  በመሆኑ  በአሁኑ ወቅት የሚቀርቡ የቃላት ምልልሶች ላይ ሰፊውን ቦታ ይዞ እንዲወጣ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ህዝብ ምን እንደምንፈልግ አላማና ግቦችን ለይቶ ማወቅ እንደሚገባ የሚገልጹት ዶክተር ጌታቸው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራቶችን ሊያሳኩ ይችላሉ ተብለው የተመደቡ  የስራ ሃላፊዎችን  በብቃት መስፈርት ብቻ  መመዘን ዘለቄታዊ ጥቅሙ የጎላ ነው ብለዋል፡፡

‘ሰው በቆዳ ከለሩ ሳይሆን ባስተሳሰቡ ይዘትና በእውቀቱ መለካት አለበት’ የሚለውን የመብት ታጋዩን ማርቲን ሉተርኪንግን አባባል በምሳሌነት የጠቀሱት ዶክተሩ የምንፈልገውን ለውጥ ለማሳካት ሰው ሲመረጥ ከአንዱ ብሄር መሆኑ  የማይቀር  እንደሆነ ነው ያስረዱት።

ወደድንም ጠላንም  የሚሾመው አመራር ከአንዱ ብሄር መሆን ግድ ነው የሚሉት ዶክተር ጌታቸው፣ ይህ ግለሰብ በብቃቱና በእውቀቱ እንጂ ሊለወጥ በማይችሉ ማንነቱ ላይ ያተኮረ ትችት ትክክል አለመሆኑን ገልፀው “ይሄ ለብዙ አመታት የኖርንበትና ስናቀነቅነው የቆየው የፖለቲካ አስተዳደር ውጤት ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አዲሱ አመራር ከዚህ አስተሳሰብ የሚያወጣን ስራ መስራት መጀመሩ መልካም በመሆኑንና በሀገሪቱ ምክንያታዊነት መዳበር  እንዳለበትም  ነው ያስረዱት። ሁሉንም ስልጣን በብሄር መነጽር ማየትን ለማስቀረት ትምህርት ቤቶችና መገናኛ ብዙሃን ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት ዶክተር ጌታቸው፡፡

በምንኖርበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ከማይቀየረው ማንነት ይልቅ ሰው ሊለይ በሚችልበት አስተሳሰብና እውቀቱ ላይ ተመስርቶ መምረጥ ግድ እየሆነ መጥቷል። በርካታ ያደጉ ሀገራትም በስደት ወደ ሃገራቸው የገቡ ነዋሪዎችን ለትላልቅ የስራ ሀላፊነት እየመረጡ መሆኑን እያየን እንገኛለን፡፡

ሰሞኑን በተካሄደው የአሜሪካ ኮንግረስ አባልነት ምርጫ ትውልዳቸው ከምስራቅ አፍሪካ የሆኑ አሌክሳንደር አሰፋ፣ ኢልሃን ኦማር እና ጆ ንጉሴ መመረጣቸው እኛ ብዙ ልንማርበት  የሚገባ ጉዳይነው፡፡ በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ታሪክም ኢልሃን ኦማር የመጀመሪያዋ ሙስሊም መሆኗንም ነው በመገናኛ ብዙሃን የተዘገበው፡፡

እኛም “ሀገር የመገንባት ብቸኛው አቋራጭና አማራጭ መንገድ ሰላም ነው” በሚለው  በፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ንግግር ሀሳባችንን ለመቋጨት ወደናል፡፡ ለምን ቢሉ?  ሰላም ከሌለ  አዲስ ሊገነባ ቀርቶ የተገነባው ይናዳልና፤ በዴሞክራሲ  ከመበልጸግ  ፋንታ አባገነንነት ይነግሳልና፡፡ ይህን የተረዱት ፕሬዚዳንቷ ለሀገር  ግንባታ ሰላም  ከሁሉም በላይ  አስፈላጊ መሆንን ያበሰሩት።  ለሰላም ሁላችንም ዘብ እንቁም፤ ቸር እንሰንብት!