ወደ ነገ የሚያሸጋግረን ስልጡን የፖለቲካ ባህል ግንባታ ያስፈልገናል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

147
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 አሁን ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ኢትዮጵያ ስትከተለው በነበረው የፖለቲካ ባህል ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአክቲቪስቶች፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ጋር 'የፖለቲካ ማሻሻያ' በሚል እየተወያዩ ይገኛል። ''እስካሁን የነበረው የፖለቲካ ጉዞ የነበረውን የማፍረስና በመጠማመድ ብሎም በመተላለፍ ላይ የተመሰረተ ነበር'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ደግሞ ከአገር ታሪክ ማስቀጠል ጋር አብሮ የማይሄድና ወደ ኋላ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል። ለአገራችን እድገት ስንል የቆየን የፖለቲካ ባህል በውይይት በምክክርና በትብብር በመቀየር ችግሮቹን አስወግዶ ወደ ፊት መጓዝ እንደሚያስፈልግም ነው ያስታወቁት። ጊዜው ብዙሃን ኢትዮጵያውያን ዋጋ ከፍለው ያመጡት ለውጥ በመሆኑ የህዝቡን ተስፋ እውን ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል። ዴሞክራሲያዊ ምርጫም የማሸነፍና የመሸነፍ ጉዳይ ሳይሆን ነፃ ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ ማረጋገጥ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ሲረጋገጥ በምርጫው የምታሸንፈው ኢትዮጵያ እንጂ ፓርቲ ብቻ አይደለም ብለዋል። ለዚህም መንግስት የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ጠንካራና ተፎካካሪ የፖለቲካ ተቋም ለመመስረት እየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም