ትምህርት በአቅራቢያችን ማግኘት ችለናል--- በሶማሌ ክልል አስተያየት ሰጪዎች

123
ጅግጅጋ ግንቦት 16/2010 ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በተደረገ ጥረት አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው  ማግኘት እንደቻሉ በሶማሌ ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአየሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ወጣት አብዲቃድር በሽር  በተወለደበት በዶሎ ዞን ደራቶሌ ወረዳ እድሜው ለትምህርት በደረሰበት ወቅት በአቅራቢያው አገልግሎቱ ባለመኖሩ  ትምህርት ቤት ሳይገባ ቆይቶ ነበር። "ቤተሰቦቼ እንድማር ካላቸው ፍላጎት 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው ዋርዴር ከተማ ልከውኝ ከዘመድ ጋር ተጠግቼ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ  ትምህርቴን ለመከታተል በቅቻለሁ " ብሏል ። በ2005 ዓ.ም. ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኢንፎሬሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት መመረቁን የተናገረው ወጣት አብዲቃድር "አሁን ላይ ያስተማረውን ማህበረሰብ ማገልገል በመቻሉ መደሰቱን ተናግሯል። አብዲቃድር እንዳለው እርሱ ተቸግሮ ቢማርም በአሁኑ ወቅት ትምህርት በመስፋፋቱና በደራቶሌ ከተማም እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  በመኖሩ ወጣቶች በአቅራቢያቸው ለመማር በመቻላቸው ትልቅ ለውጥ መጥቷል ። በክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ የስርዓተ ጾታ ስራ ሂደት አስተባባሪ ወይዘሮ ዘይነብ ሀጂ ዩሱፍ በበኩላቸው ክልሉ ከዓመታት በፊት የትምህርት  ተቋማት ያልተስፋፋበት እንደነበር አስታውሰዋል ። "እንኳን ሴቶች ወንዶችም የትምህርት እድል የማግኘት  አጋጣሚያቸው በጣም ጠባብ ነበር" ብለዋል ። አሁን ላይ በአካባቢው ትምህርት ቤቶች በመስፋፋታቸው በየቀበሌው አንደኛ ደረጃና አማራጭ ትምህርት መስጫ ጣቢያ በመገንባታቸው ሴቶች ሳይርቁ መማር መጀመራቸውን ገልጸዋል። ክልሉ ራሱን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ ትምህርት ለማህበረሰብ ለውጥና ለሀገር እድገት የሚያበረክተውን ጠቀሜታ በመረዳት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐሙድ አህመድ ናቸው፡፡ የክልሉ ትምህርት ከአርብቶ አደሩ ህይወት ጋር የተዛመደ እንዲሆንና ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በመደረጉ በትምህርት እንቅስቃሴ ስራው  ላይ የወላጆችና የተማሪዎች ተሳትፎ ማደጉንም ጠቁመዋል ። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ በዘርፉ የታየው ለውጥ የመጣው ባለፉት ዓመታት ትምህርትን ለሁሉም በፍትሃዊነት ለማዳረስ በተፈጠረው ምቹ ነው፡፡ ህብረተሰቡ የትምህርት አገልግሎት በአማካይ ቦታ እንዲያገኝ መድረጉ በክልሉ እየታየ ላለው እድገት አስተዋጽኦ  ማበርከቱንም አመልክተዋል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት በክልሉ ከ3ሺህ በላይ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 10 ኮሌጆችና ሁለት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም