የማዕድን ሥራዎች ምክር ቤት ሊቋቋም ነው

72
አዳማ ህዳር 14/2011 በማዕድን ዘርፍ ያሉትን ማነቆዎች ለማስወገድ እንዲቻል የማዕድን ሥራዎች ምክር ቤት ሊቋቋም መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሀገር አቀፍ የማዕድን ሥራዎች ምክር ቤት ምስረታና አንደኛ መደበኛ ልዩ ጉባኤ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል። የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ሁርጶ  በዚህ ወቅት እንደገለጹት የማዕድን ሃብት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገትና ለህብረተሰቡ ኑሮ መሻሻል ያበረከተው ድርሻ ዝቅተኛ ነው። ለዘርፍ በሚገባ አለማደግ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እንዳሉበት ያመለከቱት ሚኒስትሩ በተለይ ተቋማዊ የመምራት አቅምና ብቃት አለመገንባት ዋንኛው እንደሆነ ተናግረዋል። የማዕድን ሃብት በጥናትና ምርምር ተደግፎ  ዘመናዊ የማዕድን አለኝታ መረጃ በማደራጀት ለኢንቨስትመንት ዕድል እንዲተዋወቅ አልተደረገም፡፡ በዚህም ምክንያት ገበያ መር በሆነ ውድድር ሀገር በቀልና የውጪ ባለሃብቶችን በዘርፉ በበቂ ሁኔታ እንዳልተሰማሩ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት  በብቃትና በውጤታማ የአጠቃቀም ሥርዓት ለመምራት የሚያስችሉ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ፣ የዘርፉን የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ አለመደራጀት የማዕድን ሀብቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳይውል ረጅም ዓመታት መቆየቱንም አስረድተዋል። ህገወጥ የማዕድን ልማትና ግብይት በመስፋፋቱም ህዝቡና ሀገሪቱ የዘርፉን ጥቅም በፍትሐዊነት፣ በግልጸኝነትና በተጠያቂነት ለመጠቀም እንዳልታደሉም ጠቁመዋል፡፡ በማዕድን ዘርፍ ያሉትን ማነቆዎችን ማስወገድ እንዲቻል የማዕድን ሥራዎች ምክር ቤት በሚኒስተሮች ምክር ቤት እንዲቋቋም መወሰኑን አስታውቀዋል። በሚኒስቴሩ የህግ አገልግሎት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ በአምላክ አለማየሁ በበኩላቸው የሚቋቋመው የማዕድን ሥራዎች ምክር ቤት  ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ገልጸዋል። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ የክልል የማዕድን ቢሮዎች፣  የክልል የአካበቢና የደን ጥበቃ አካላት ይገኙበታል። የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣የገቢዎች፣ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴሮች፣በማዕድን ዘርፍ የጎላ ሚና ካላቸው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፣መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ከማዕድን ሥራዎች ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የሙያ ማህበራትም ተካተዋል። ምክር ቤቱ የማዕድን ዘርፍ ከወቅቱ ዓለም አቀፍ የማዕድን ኢንዱስትሪው ጋር ተወዳዳሪ በማድረግ በዘርፉ የግል ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ዘላቂ የሆነ ሀገራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ የሚያስችል የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ ሀሳቦችን ለሚኒስትሩ የማቅረብና የማማከር ተግባርና ኃላፊነት እንደተጣለበት አስታውቀዋል። የማዕድን ሀብት ውስንና አላቂ በመሆኑ በህግ ማዕቀፍ ሊመራ እንደሚገባው ያመለከቱት  ደግሞ የማዕድን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰፋ ኩምሳ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ችግር ውስጥ የወደቀውን የማዕድን አጠቃቀምና ብክነት ሥርዓት ለማስያዝ የምክር ቤቱ  መቋቋም ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው ጉባኤ  ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ  ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም